“መደመር”መፅሃፍ ተመረቀ

በጠ/ሚዶ/ር ዐብይ አህመድ የተፃፈው መደመር”መፅሃፍ በዛሬው ዕለት ተመረቀ፡፡

መፅሃፉ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በ30 የክልል ከተሞች ተመርቋል፡፡

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት፣ ነዋሪዎችና የሀይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው በዚህ የምረቃ ስነ ስርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ፣ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም ከ8 ሺህ በላይ የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

በ300 ብር በሶስት ቋንቋዎች ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች የቀረበው መፅሃፉ 287 ገፆችን የያዘ ሲሆን በ16 ምዕራፎችና በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ መጽሃፉ በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና እንግሊዘኛ የታተመ ነው፡፡

የሰው ተፈጥሮና ፍላጎት፣ፐለቲካዊ ጉዳዮች፣ የውጭ ግንኙነት እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም በመፅሃፉ በስፋት ተዳስሰዋል፡፡

ከመፅሃፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ትምህርትቤቶችን ለመገንባት እንደሚውል በመፅሃፉ ሽፋን ተመልክቷል፡፡

መፅሃፉ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን የሚያበረታታ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የምረቃ ስነስርዓቱ የየአካባቢውን ባህል ባገናዘበ ሆኔታ እንደሚካሄድም ነው የተገፀው፡፡

በተጨማሪም መፅሃፉ በውጭ ሀገራት የሚመረቅ ሲሆን በዋናነትም በአሜሪካ እና ኬንያ በተለይም በዋኝንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ሚኒሶታ እና ናይሮቢ የሚመረቅ ይሆናል፡፡