ኢትዮጵያን በአፍሪካ ታላላቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እየተከናወኑ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጅቡቲ የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ዝግጅት ላይ በድንገት በመገኘት ባሰሙት ንግግር መንግስት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ታላላቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት አንዷ እንድትሆን እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 ኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን አስመልክቶ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት የተሰናዳ የደስታ መግለጫ ፕሮግራም ላይ በድንገት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓሉ ታዳሚ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ንግግር አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ‹‹ይሄ የሚገርም ግጥምጥሞሽ ነው… ዳያስፖራው ዝግጅት አለው ሲባል ሰላምታ ለማቅረብ ነው የመጣሁት›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹በጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚለዩበት አንድ መለያ በሰላም መኖር፣ የአገሪቱን ህግ ማክበር፣ ስራ መውደድ፣ እርስ በእርስ መግባባት፣ የተቸገረን መርዳት ሲሆን ሁሌ የምትመሰገኑበትን ይሄንን መልካም ስማችሁን እንድታቆዩ አደራ እላችኋለሁ›› ብለዋል፡፡

ጅቡቲ ሁለተኛ ቤታችን ነው ያሉት ዶ/ር ዐቢይ መደመር በጅቡቲ እና በኢትዮጵያ በግልጽ መታዩት ጠቅሰዋል::

ይሄንን በሁለቱ አገራት መካከል ያለ ጥብቅ ወዳጅነት የምታጠናክሩ ድልድዮች ጀግና ኢትዮጵያውያን ስለሆናችሁ በታማኝነት፣ በጨዋነትና በፍቅር እዚህ ካለው ህዝብ ጋር በመኖር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር እያንዳንዱ ዜጋ እንደ አምባሳደር እንዲሰራም አደራ ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማቱ በአንድ ሰው ስም መነገር ስላለበት እንጂ ሽልማቱ የሁላችሁም ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና የጅቡቲ፣ የሶማሊያ፣ የሱዳን፣ የኤርትራ ብልጽግና መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በውስጣችንም በአጎራባች አገራት ሰላም እንዲኖር እንሰራለን ብለዋል፡፡

በሚቀጥለው ምርጫ ከተመረጥን እንሰራለን ካልተመረጥን አቅፈን በማስረከብ አርዓያ የሆነ ስራ እንሰራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ተሸንፎ ስልጣንን በስርዓት ማስረከብ ከዚህ ኖቤል የሚበልጥ እንጂ የሚተናነስ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ስደት እንዲያበቃ ለትውልዶች የምትበጅ ኢትዮጵያን ሰርቶ ማቆየት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በጅቡቲ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉስልጣን አምባሳደር አብዱልአዚዝ መሐመድ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለዚህ ታላቅ ዓለም-አቀፋዊ ሽልማት በመብቃታቸው በጅቡቲ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል::

ሽልማቱ መላው ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ከመሆኑም ባሻገር አገሪቱን በዓለም-አቀፍ መድረኮች ላይ እየተጫወተች ያለውን ሚና የሚያጎላና እውቅናንም የሚሰጥ እንደሆነም ተናግረዋል::

(ምንጭ:- በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ)