በመለስ ፋውንዴሽን የተመረጡ 83ተማሪዎች የኮምፒተር ሳይንስ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 27/2008 (ዋኢማ) – በመለስ ፋውንዴሽን ከመላ አገሪቱ የተመረጡ 83 ተማሪዎች የኮምፒተር ሳይንስ ከውጭ አገር በመጡ ምሁራን ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑ ተመለከተ ፡፡

በዚሁ ከሓምሌ 1/2008 ዓመተ ምህረት አንስቶ ለአንድ ወር እየተሰጣቸው ያለው ስልጠና ከሁሉም ክልሎች፣ ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች በሒሳብ ችሎታቸው የላቀ ውጤት ያመጡ ተመናሪዎች መሆናቸው ተገልጿል ፡፡

በአሜሪካን አገር ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪዋን እያጠናች ያለችው በጎ ፈቃደኛ ወጣት ትምኒት ገብሩ ከፋውንዴሽኑ ጋር በመገናኘት ያላትን ዕውቀት ለሀገሯ ልጆች ለማበርከት ከጓደኛዋ ጋር ተማክራ መምጣቷን አስረድታለች ፡፡

ተማሪዎቹ ባብዛኛው ኮምፒውተር ነክተው የማያውቁ ቢሆንም ባጭር ጊዜ ኮምፒውተርን ተምረው ስልጠናውን በአግባቡ እየተከታሉ መሆኑን አብራርታለች ፡፡

እንደዚሁም ኮምፒውተር ሳይንስ ሰፊ ዕድል እንዳለው አያውቁም ነበር ያለችው ወጣት ትምኒት ፤ዘርፉ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ አስፈላጊ ስልጠና እንደሆነ እንዲያውቁ እየተደረገ መሆኑን አስታውቃለች  ፡፡

በቀጣይ ዓመትም ተመሳሳይ ስልጠና ለመስጠት ከሌሎች በጎ ፍቃደኞች ጋር እንደሚመጡ ጠቁማ፤ስልጠናው ከመጀመሩ በፊት በኮምፒውተር መጻፍ የማይችሉ ተማሪዎች አስቀድሞ ልምምድ እድርገው ቢዘጋጁ የተሻለ መሆኑን አመልክታለች ፡፡

ከሰልጣኛቹ ውስጥ በሐዋሳ ከተማ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ቤተልሔም ደሳለኝ በሰጠችው አስተያየት የወደፊት ዓላማዋ የህክምና ሳይንስ ዶክተር ለመሆን የነበረ ቢሆንም ስልጠናው ዓላማዋ እንድትቀይር ስለአደረጋት የኮምፒውተር ሶፍትዌር እንጂነር ለመሆን እንደምትፈልግ ገልጻለች  ፡፡

ሌላው ከሐረር ከተማ የመጣው የ12ኛ ክፍል ተማሪ መአድን ስይድ በበኩሉ እንዳመለከተው፤ ከዚህ በፊት ስለኮምውተር ሳይንስ ሃሳቡም ዕውቀቱም እንዳልነበረው ገልጾ፤ አሁን ከኮምፒውተር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በቀጣይ የጠፈር ተመራማሪ በመሆን ሀገሩን በስነ ኮዋክብት ያላትን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ማለሙን አስረድቷል ፡፡

የስልጠናው ዓላማ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ስለኮፒውተር ፕሮግራም  በማለማመድ በሄዱበት ቦታ ለሌሎች ተማሪዎች ዕውቀታቸውን እንዲያካፍሉ መሆኑን ታውቋል ፡፡