ስጋ አብዝቶ መመገብ የመሞት እድልን ያሰፋል – ጥናት

አዲስ አበባ ሐምሌ 27/2008(ዋኢማ)-አብዛኛዎቹ ሰዎች በፕሮቲን የበለጸገ ምግብን መመገብ ቀዳሚ ምርጫቸው ያደርጋሉ።

ስጋን ጨምሮ በፕሮቲን የበለጸጉ አትክልትና ጥራጥሬዎች ደግሞ በዚህ መልኩ ተጠቃሽ ምግቦች ናቸው።

ከዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው ስጋ በተለይም ጥሬ ስጋ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ እና የሚዘወተር ምግብ ነው።

ከዚህ ባለፈም በስጋ የሚሰሩ የተቀነባበሩ ምግቦችም በወጣቶች ዘንድ ይዘወተራሉ።

ይህ መሆኑ ግን የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ነው ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የሚናገሩት እና የሚያስጠነቅቁት።

በሃገረ አሜሪካ ማሳቹሴትስ ሆስፒታል የሚገኙ ተመራማሪዎች ደግሞ በዘርፉ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የተደረገ ጥናትን ውጤት ይፋ አድርገዋል።

ጥናቱ በ131 ሺህ 342 ሰዎች ላይ፥ የሰዎቹን የቀን የፕሮቲን የፍጆታ መጠን እና የፕሮቲኑን ምንጭ ተንተርሶ የተደረገ ነው።

ተመራማሪዎቹ የሰዎቹን ስጋና የስጋ ተዋጽኦዎችን አመጋገብ መነሻ በማድረግ ነበር ጥናቱን ያደረጉት።

በዚህም አብዝቶ ስጋን እና የተቀነባበሩ የስጋ ውጤቶችን መመገብ የሞት ተጋላጭነትን ይጨምራል ብለዋል።

ይህ ደግሞ ስጋ ተጠቃሚው ሰው ምናልባትም ከፍተኛ መጠጥ እና ሲጋራ ተጠቃሚ የነበረና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማያደርግ ከሆነ ተጋላጭነቱን እንደሚያሰፋውም አንስተዋል።

እንደ ጥናቱ ምናልባት ግለሰቡ/ግለሰቧ ከፕሮቲን ፍጆታቸው 10 በመቶ ያህሉን ከስጋ የሚያገኙ ከሆነ፥ በጤና የመሰንበትና በህይዎት በየመቆየት እድላቸው በ2 በመቶ ይቀንሳል።

ከዚህ ባለፈም ለልብ እና ተያያዥ የጤና እክሎች የመጋለጥ እድላቸው በ8 በመቶ ከፍ ይላልም ነው ያሉት።

ከዚህ በተቃራኒው ግን የፕሮቲን ፍጆታቸውን ከአትክልትና ጥራጥሬ የሚያገኙ ከሆነ ደግሞ፥ የመሞት እድላቸውን በ10 በመቶ ሲቀንሱ ለልብ እና ተያያዥ የጤና ችግሮች የመጋለጥ እድላቸውም በ12 በመቶ ይቀንሳል።

የእንስሳት ተዋጽኦ የሆነው የስጋ ፕሮቲን የኢንሱሊን መጠንን ከፍ ስለሚያደርገው ለዚህ ችግር ይዳርጋል ይላሉ የጥናት ቡድኑ መሪ ዶክተር ሚንግያንግ ሶንግ።

ሂደት የበዛባቸው የስጋ ተዋጽኦወች ደግሞ በሶዲየም እና ናይትሬትስ የበለጸጉ እንደመሆናቸው፥ የጤና እክል እንደሚያስከትሉም ይናገራሉ።

እናም ይላሉ እርሳቸው ስጋዎችንና የስጋ ተዋጽኦዎችን አብዝቶ በመመገብ ጤናን ከመጉዳት፥ የፕሮቲን ይዘታቸው ከፍ ያሉ አትክልት እና ጥሬጥሬዎችን መመገብ።

ለዚህ ደግሞ እንደ ባቄላ እና መሰል ጥራጥሬዎችን እና ለውዝ አይነት የአትክልት ዘሮችን መጠቀም መልካም መሆኑን ይመክራሉ።(ኤፍ ቢ ሲ)