ኮሚሽኑ የተከሰተው ድርቅ ተፅእኖ እየቀነሰ መምጣቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6/ 2008(ዋኢማ)- ባለፈው ዓመት በሀገራችን የተከሰተው ድርቅ የተጽእኖ መጠን እየቀነሰ መምጣቱን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ ።

ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ባለፉት የበልግ ወራት ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን በመዝራት ምርት እንዲገኝ ሲደረግ በመቆየቱ ድርቁ ያስከተለው ተጽእኖ እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል።

በየአከባቢው በተሰሩ የማገገሚያ ስራዎች ተረጂዎች ራሳቸውን እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ።

እንደ ማሳያም በአማራ ክልል በዚህ ስራ በሶስት ወራት ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን አንስተዋል።

አሁን ላይ ባለው የክረምት እና ቀደም ብሎ በገባ የበጋ ወቅት ምርት አርሶ አደሩ እያገገመ እንደሚገኝ አስረድተዋል ።

በተለይም በድርቅ በተጎዱ አከባቢዎች የነበነረው የውሃና የእንስሳት መኖ እጥረት በበልግና ክረም ዝናብ ምክንያት መቃለሉን ጠቅሰዋል ፡፡

የበልግና የመኸር ምርት ያገኙና የሚያገኙ አከባቢ ላይ ያሉ ተረጂዎች የልየታ ዳሰሳ ተደርጎ የተጠናቀቀ መሆኑንና ምን ያክል አገግሟል የሚለው ቁጥር በቅርቡ እንደሚገለጽ አመልክተዋል ።

አቶ ምትኩ ዳሰሳው ባሳየው ጥቆማ የቀጣይ ተረጂዎች ቁጥር በሚያገኙት ምርት ላይ ተሞርኩዞ አሁን ካለው 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊቀንስ እንደሚችልም ገልጸዋል።

ይህ ማለት ግን ተረጂዎቹ ምርት ሳያገኙ ድጋፉ ይቋረጣል ማለት አይደለም ብለዋል ፡፡

ላለፉት ተከታታይ ወራት በ1 ሺህ 900 የእርዳታ ጣቢያ በኩል ሲደረግ የነበረው ድጋፍ አሁንም መቀጠሉን ነው ኮሚሽነሩ ያነሱት።

አሁን በክምችት ብቻ 451 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ያለ ሲሆን በቀጣዮቹ 15 ቀናት ውስጥ ወደብ የሚደርስ 499 ሺህ 536 ሜትሪክ ቶን ስንዴ በግዢ ሂድት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል።

ከጥራጥሬ፣ ዘይትና መሰል ምርቶች ጋር ተያይዞ ምንም አይነት እጥረት እንደሌለም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

እስካሁን ድረስ በተለያዩ መንገዶች ለተረጂዎቹ ከ16 ቢሊየን ብር በላይ መንግስት ወጪ ማደረጉን ከብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ አመልክቷል ።

ወጪው ህብረተሰቡ፣ ባለሀብቱና የክልል መንግስታት ያደረጉትን አስተዋጽኦን ሳያካትት መሆኑም ታውቋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።