በአገሪቱ አስቸኳይ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ተረጂዎች በግማሽ ሚሊየን ይቀንሳል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2008 (ዋኢማ)-በቀጣዮቹ አምስት ወራት አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተረጂዎች ቁጥር በ499 ሺህ 424 እንደሚቀንስ ተገለጸ።

ይህን የገለጸው የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በበልግ አብቃይና አርብቶ አደር አካባቢዎች በበልግ አብቃይና በአርብቶ አደር አካባቢዎች በተካሄደ የምግብ ዋስትና የዳሰሳ ጥናት በማካሄዱ ነው ።

ጥናቱ በሰብል አብቃይ አካባቢዎች ከግንቦት 28 እስከ ሰኔ 12 ቀን 2008 ዓ.ም፤ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ደግሞ ከግንቦት 28 እስከ ሰኔ 18 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ማካሄዱን ኮሚሽኑ አመልክቷል ።

የወቅቱ የዝናብ ሁኔታ፣ የእርሻ ስራ እንቅስቃሴ፣ በማሳ ላይ ያለው ሰብል፣ የምርት ግምት፣ የግጦሽና የውሃ አቅርቦት፣ የእንስሳት አቋምና ምርት ሁኔታ፣ የሰውና የእንስሳት ጤና በጥናቱ ተዳሷል።

በወቅቱ እየተሰራጨ ያለው የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች የስርጭት ሁኔታና የማህበረሰቡ የምግብ ዋስትና ሁኔታም ተገምግሟል።

ከጥናቱ በተገኘው ውጤት መሰረት ቀደም ሲል ከነበረው 10 ሚሊዮን 241 ሺህ ተረጂ ከነሐሴ 2008 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2009 ዓ.ም ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች ድጋፍ የሚያስፈልገው ወደ 9 ሚሊዮን 741 ሺህ 576 እንደሚቀንስ ተረጋግጧል።

ለ15 ቀናት በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ሰብል አብቃይ በሆኑ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች 19 ቡድኖች መሳተፋቸውን አስታውቀዋል ።

ከአርብቶ አደር አካባቢዎች በአፋርና በሶማሌ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በቦረናና ጉጂ ዞኖችም ለ21 ቀናት መካሄዱንም ጠቁሟል ።

ጥናቱን በኮሚሽኑ አስተባባሪነት የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የክልል ሴክተር ቢሮዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች፣ የሁለትዮሽ ስምምነት ያላቸውና መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተሳትፈውበታል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው ።