የጤና ግቦችን ለማሳካት ማህበሩ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ፕሬዝዳንቱ ገለፁ

ነሐሴ 17/2008 (ዋኢማ)- ኢትዮጵያ የምዕተ ዓመቱን የጤና ግቦች ለማሳካት ባደረገችው ጥረት የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር ዓይነተኛ ሚና እንደተጫወተ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለፁ፡፡

ማሕበሩ ዛሬ የምስረታውን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ሲያከብር ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ በይፋዊ መክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት ማህበሩ የጤና ፖሊሲዎችን ባገናዘበ መልኩ ያበረከተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው፡፡

በሥነተዋልዶ ትምህርት፣ የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚነት፣ የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ሥርጭትን  እንዲሁም በወሊድ መቆጣጠሪያ ዘርፎች ማህበሩ ጉልህ ተግባራት ማከናወኑን ፕሬዚዳንቱ ተናረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አክለው እንደገለጹት የእናቶችን ሞት ወደ 12 በመቶ በመቀነስ፣ በሕይወት የመኖር ዕድሜን ወደ 64 በመቶ ከፍ በማድረግ፣ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚነትን 42 በመቶ እንዲሁም አማካይ የውልደት መጠንን 4 ነጥብ 1 በማድረስ ኢትዮጵያ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ቀድማ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች አሳክታለች፡፡

ማህበሩ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር በተለይም የማህበራዊ ቢዝነስ ኢንተርፕራይዝ እንዲሆን ለማስቻል መንግስት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንት ሙላቱ ገልጸዋል፡፡

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ ቅጣው በበኩላቸው ማሕበሩ በውጤታማ የጤና ፖሊሲ በመመራት ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት የእናቶችና ሕፃናት ሞት፣ የቲቢ፣ ወባና የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ሥርጭትን ለመቀነስ ችሏል ብለዋል፡፡

ማህበሩ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በሶስት ግለሰቦች መመስረቱን ያስታወሱት ወይዘሮ መዓዛ አሁን ከ18ሺ በላይ በጎ ፈቃደኛ አባላት እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ በተለይም የመንግስትን የጤና ፖሊሲ መርሆችን በመከተል በማህበረሰብ አቀፍ ጤና ፕሮግራሞች ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በመግለጫው ላይ እንደተመለከተው ማህበሩ በጤናው ዘርፍ በሰራቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት በአፍሪካ  አምስት አገሮች ከተመረጡ ተመሳሳይ ማህበራት ተርታ ለመሰለፍ በቅቷል፡፡

ማህበሩ ከ90 በመቶ ያላነሰ ገቢውን ከውጭ በጎ አድራጊ ድርጅቶች እንደሚያገኝና በቀጣይ የማህበራዊ ቢዝነስ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ገቢ ከአገር ውስጥ ለማግኘት ማቀዱን ፕሬዝዳንቷ ጠቁመዋል፡፡

ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ካሉት ክሊኒኮች፣ አገልግሎት መስጫ ማዕከሎችና በጎ ፈቃደኞች የገቢ ምንጩን ለማሳደግ ይሰራል ተብሏል፡፡ አቅም ለሌላቸው ዜጎች አገልግሎቱን በነፃ እንደሚሰጥም ነው የተመለከተው፡፡

ማህበሩ ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አውጥቶ እየሰራ እንደሆነ ፕሬዚዳንቷ አስታውሰው በቀጣይም የማሕጸን ጫፍ በር ካንሰር ሕክምና ከተ ችግሩ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ እንዲቻል ትኩረት ሰጥቶ ለመንቀሳቀስ አቅዷል፡፡

በዕለቱ አውደርዕይ፣ ጥናታዊ ጽሁፎች እንዲሁም በ50 ዓመታት ውስጥ የተከናወኑ ዓበይት ተግባራትን የሚዘክር ዘጋቢ ፊልም ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም ለማህበሩ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች የምስጋና ሽልማትና ሰርቲፊኬት እንደተበረከተላቸው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡