ድርጅቱ በአፍሪካ ድንገተኛ በሽታዎችን ለመከላከል የሚውል በጀት አፀደቀ

ነሐሴ 17/2008(ዋኢማ)- የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ ለሚከሰቱ ድንገተኛ በሽታዎች መከላከያ የሚውል 106 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር በጀት አፀደቀ።

ገንዘቡ ድንገት የሚከሰቱ በሽታዎችን በመከላከል በአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

የድርጅቱ የአፍሪካ ተወካይ ዶክተር ማቲሺዲሶ ሞኢቲ እንዳሉት በጀቱ የአህጉሪቱን የጤና ዕቅዶች ለመተግበርና በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ አስቸኳይ በሽታዎችን ለመከላከል ይውላል።

በአህጉሪቱ የሚከሰቱ ድንበር ዘለል በሽታዎች ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን ዕቅድ ለመተግበርም ከፍተኛ እገዛ አለው ነው ያሉት።

በአፍሪካ በየዓመቱ ከ100 በላይ አስቸኳይ የመከላከል እርምጃ የሚፈልጉ ድንገተኛ በሽታዎች ይከሰታሉ።

ከእነዚህ መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በተለያዩ ኢንፌክሽኖች፣ 18 በመቶዎቹ በተፈጥሮ አደጋ ሲከሰቱ ቀሪው ሁለት በመቶ በኬሚካሎች መመረዝ የሚመጡ ናቸው።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ የጤና ጉባኤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ በሚደረግ በጀትና በአህጉሪቱ የጤና ጉዳዮች ላይ መክሯል።

የዓለም የጤና ድርጅት ምክትል ዳሬክተር ዶክተር ሃናስ ትሮድሰን ድርጅቱ ለ2018 እና 2019 ዓመት ለጤናው ዘርፍ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በጀት መመደቡን ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላሩ በአፍሪካ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደሚውል ነው ያስታወቁት።

በጀቱ በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት 2017 ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡