በዋቢ ሸበሌ ወንዝ ላይ የተገነባውና 97 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኤረር ዞን በዋቢ ሸበሌ ወንዝ ላይ የተገነባውና 97 ሜትር ርዝመት ያለው ዋንጋይ ድልድይ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ ።

በአንድ ጊዜ ሁለት ተሽከርካሪዎችን እንዲያስተላልፍ ተደርጎ የተሰራው ይህ ድልድይ ቀደም ሲል 3 ሺ ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠይቅ የነበረውን መንገድ ወደ 60 ኪሎ ሜትር ማሳጠሩ የተለየ ያደርገዋል ተብሏል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀሙድ ዑመር ከትናንት በስተያ ድልድዩን ሲመርቁ እንደገለጹት፣ ድልድዩ የተገነባው በክልሉ ኤረር ዞን በሚገኙ ሰላሀድ፣ ለገሂዳ፣ ቁቢና ሀመሮ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለዘመናት የነበረባቸውን የትራንስፖርት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ታስቦ ነው።

ድልድዩና ከድልድዩ ግራና ቀኝ የተገነባው 30 ኪሎ ሜትር ጥርጊያ መንገድ ቀደም ሲል የአካባቢው አርብቶ አደሮች የቁም እንስሳት፣ የእንስሳት ተዋፅኦ እንዲሁም የማርና ሌሎች የግብርና ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ የነበረባቸውን የገበያ ችግር ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የክልሉ መንግስት የአካባቢውን ነዋሪዎች በልማትና በመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ለሚያደርገው ጥረትም ድልድዩ የራሱ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አቶ አብዲ አመልክተዋል፡፡

ከትናንትና በስተያ  ዕለት ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው ድልድይ ቀደም ሲል ከሀመሮ ወደ ሰላሀዲ ወረዳ ለመድረስ ሐረር፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ሲቲ ዞን፣ አፋር ክልል፣ ምስራቅ ሸዋና ባሌ ዞኖችን በማቋረጥ ይደረግ የነበረውን የ3 ሺ ኪሎ ሜትር ጉዞ ወደ 60 ኪ.ሜ እንደሚያሳጥረው ተገልጿል።

በክልሉ መንግስት ልዩ ፖሊስ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ አማካኝነት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የዋንጋይ ድልድይ ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ  ወጪ ተደርጎበታል።

ግንባታው 17 ወራትን የፈጀው ይህ ድልድይ ለአካባቢው የመጀመሪያ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ኢድሪስ ኢስማኢል ተናግረዋል፡፡(ኢዜአ)