አዲስ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ሊወጣ ነው

አሁን በሥራ ላይ ያለውን የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ የሚተካ አዲስ አዋጅ ሊወጣ መሆኑ ተመለከተ፡፡

አዲሱ የብሮድካስት አዋጅ የብሮድካስት አገልግሎቱን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ለመለወጥ የሚደረገውን ሽግግር ለማሳለጥ የሚረዳ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ለዋልታ አስታውቋል፡፡

አዲሱ አዋጅ የዲጂታል አገልግሎት ፍቃድ ለማግኘት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችና ሌሎች ከዲጂታል አገልግሎት ጋር የተያያዙ የተለያዩ የህግ ድንጋጌዎችን አካቶ የተዘጋጀ መሆኑን በባለሥልጣኑ የመገናኛ ብዙኃን ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ሲሳይ ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

‹‹አሁን የብሮድካስት አገልግሎቱ አናሎግ በመሆኑ ፍቃድ የሚሰጠውም ለዚህ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ነው›› ያሉት አቶ ሙሉጌታ የቴሌቭዝን ጣቢያዎች ወደ ዲጂታል እንዲሸጋገሩ እየተሰራ በመሆኑ መስፈርቱም ይለያል ብለዋል፡፡ ለዚህም አዲሱ አዋጅ የዲጂታል ሥርዓቱን ባገናዘበ መልኩ እንዲዘጋጅ ተደርጓል ብለዋል፡፡

አዋጁ አሁን በሥራ ላይ ያለው የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ያሉበትን ክፍተቶች በመሙላት የዲጂታል ሽግግሩን እንደሚያግዝም ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት፡፡

በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተገቢው ውይይትና ምክክር መደረጉንም ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም አዲሱ አዋጅ ከሌሎች ህጎች ጋር መጋጨትና አለመጋጨቱ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ የህግ ባለሙያዎች ሰፊ ውይይት አድርገውበታል፡፡ ከመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ጋር መጣጣምና አለመጣጣሙ በሚመለከታቸው አካላት በደንብ ታይቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችም በረቂቅ ደረጃ ያለውን አዋጅ እንዲያውቁት መደረጉን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የግል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን ያሳተፈ መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡ ሁሉም ብሮድካስተሮች፣ የመፅሔትና ጋዜጣ አታሚዎችም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይተዋል፡፡

በረቂቅ ደረጃ ያለው አዋጅ በሚመለከታቸው አካላት በደንብ ታይቶና ተመክሮበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲፀድቅ አሁን በሥራ ላይ ያለውን የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር533/1999 ሙሉ በሙሉ ይተካል ተብሎ ይጠበቃል፡፡