ወጣቱ ትውልድ የገዳ ሥርዓትን ጠብቆ ማቆየት እንዳለበት ተገለጸ

ወጣቱ ትውልድ በዩኔስኮ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበውን የገዳ ሥርዓትን ይበልጥ  በማሳደግና ጠብቆ ማቆየት እንዳለበት በ11ኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ ።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ለዋልታ በሠጡት አስተያያት  ወጣቱ  ትውልድ የአገር አኩሪ ባህልና እሴት የሆነውን  የገዳ ሥርዓትን  ጠብቆ በማቆየት ረገድ ተገቢውን ሚና መጫወት ይገባዋል ብለዋል ።

እንደ አቶ ዮናስ ማብራሪያ ኢትዮጵያ የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ መዝገብ ላይ እንዲሰፍር ለማድረግ ከ 3 ዓመት ተኩል በላይ  ጥረት ማድረጓን  በመጠቆም  ቅርሱ  ይበልጥ  ለምቶ ለትውልድ እንዲተላላፍ በማድረግ በኩል ወጣቱ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል ።

ወይዘሮ አሊፊያ ሃጂ በበኩላቸው ለዘመናት የአሮሞ  ህዝብ ሲጠቀምበት የነበረው  የገዳ ሥርዓት በዓለም እውቅና እንዲያገኝ በመደረጉ እጅጉን መደሰታቸውን በመገልጽ ወጣቱ ትውልድ  የማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ዴሞክራሲ መገለጫ የሆነውን ባህል ይበልጥ  የማበልጸግ  አደራውን  መቀበል እንዳለበት ተናግረዋል ።

የገዳ ሥርዓት ከባህልነት ባሻገር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተምሳሌት መሆኑን  የሚናገሩት ወይዘሮ  አሊፊያ ለህብረተሰብ የማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ መሥጠት የሚያስችል አሠራሮች  ያሉት በመሆኑና ሥርዓቱ ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ እንኳን ለአገሪቱ ወጣቶች ለመላው ዓለም ህዝቦች በምሳሌነት የሚወሰድ መሆኑን አስረድተዋል ።

በተጨማሪም የማቲ አባገዳ ደንቦባ አጋ እንደገለጹት የገዳ ሥርዓቱ በዩኔስኮ መመዝገቡ ሥርዓቱን ለወደፊቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላላፍ በማድረግ መልካም አገጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ  ወጣቱ ትውልድ የሥርዓቱን ቱፊቶችን ለመቀበል ከአባ ገዳዎች ለመማር ዝግጁ  በመሆን ታሪክ መሥራት ይኖርበታል ብለዋል ።

ሌላው በጉባኤው  ላይ  ተሳታፊ  ለማ ገመቹ እንደሚለው የገዳ ሥርዓት  የሰላም፣የአንድነት፣ የፍቅርና የመከባባር  ምሳሌ  በመሆኑ ምክንያት  ለአገር   ጠቃሚ  እሴትነቱ  የላቀ መሆኑንና    የገዳ ሥርዓትን የሚያስተምሩ  ተቋማት ተፈጥረው በተለይ ለወጣቱ ትውልድ እንዲማርበት ቢደረግ የተሻለ እንደሚሆን ተናግሯል ።