በደቡብ ከመኸር የአዝዕርት ምርት 42 በመቶ የሚሆነው ተሰበሰበ

በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በመኸር የምርት ወቅት 42 በመቶ የሚሆነው የአዝዕርት ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመኸር ወቅት በዘር መሸፈኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማሜ ጋሩማ ለዋልታ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም 29 ሚሊዮን የአዝዕርት ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አስገንዝበዋል፡፡

በዘር ከተሸፈነው መሬት 60 በመቶ የሚሆነው ምርት ለመሰብሰብ መድረሱን አቶ ግርማሜ ጠቁመው እስከ አሁን 42 በመቶ የሚሆነው መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡ ቀሪውን ቶሎ ለመሰብሰብ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሰውን ሰብል እንዳያበላሽ ‹‹በማሽንና በሠው ኃይል በመታገዝ ሰብሉን የመሰብሰብ ርብርብ እየተደረገ ነው›› ብለዋል፡፡

የተሰበሰበው ምርትም ከመወቃቱ በፊት እንዳይበላሽ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ በዘርፉ ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮቹ ግንዛቤ የመስጠትና ድጋፍ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡

ከአዝዕርቶች በተጨማሪ 40 ሚሊዮን ኩንታል የሥራ ሥር ምርቶች ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ግርማሜ ተናግረዋል፡፡ እስከ አሁንም የስኳር ድንችና ድንች ምርት መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡

በምርት ዘመኑ 186ሺ ኩንታል ምርጥ ዘርና ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በምርት ዘመኑ የታቀደውን ምርት ለማግኘት እንደሚቻል በቅርቡ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ለማረጋገጥ መቻሉም ነው የተነገረው፡፡

ለዚህም ለሰብሎች ተስማሚና ምቹ የአየር ሁኔታ መኖር፣ ጥሩ የግብዓት አጠቃቀም፣ ተገቢና ወቅታዊ የባለሙያዎች ድጋፍና ትብብር እገዛ ማድረጉን አቶ ግርማሜ ገልፀዋል፡፡ የሰብል በሽታ አለመከሰቱና በተወሰነ መልኩ ተከስቶ የነበረውም ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ዕቅዱ ግቡን እንዲመታ አድርጓል፡፡

አመራሩና ባለሙያውም ተገቢውን ዝግጅት በማድረግና ሥልጠና በመውሰድ ወደ ሥራ መግባቱም ለዕቅዱ ስኬት የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከቱ ተጠቅሷል፡፡ መድኃኒቶች እስከ ቀበሌ ድረስ እንዲሰራጩ የተደረገ ሲሆን አርሶ አደሩም አረሞችን ቶሎ ቶሎ በመንቀልና በማስወገድ የተሻለ ምርት እንዲሰበሰብ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡

ዘንድሮ የሚሰበሰበው 29 ሚሊዮን የአዝዕርት ምርት አምና ክልሉ በተመሳሳይ የምርት ወቅት ከሰበሰበው 18 ሚሊዮን ኩንታል ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡