የአክሱም ሐውልት የተገጠመለት የንዝረት መቆጣጠሪያ መበላሸቱን ባለስልጣኑ አስታወቀ

የአክሱም ሐውልት የተገጠመለት የንዝረት መቆጣጠሪያ ብልሽት እንዳጋጠመው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ ፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለ ስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ እንደገለጹት፤ የተገጠመለት የንዝረት መቆጣጠሪያ በጊዜ ብዛት በፀሀይና በዝናብ ምክንያት ብልሽት ገጥሞታል ።

ይኸው 24 ሜትር ርዝመት ያለውና "ሦስት ሐውልት" ተብሎ የሚጠራውን የአክሱም ሐውልት መቆጣሪያ ለማደስ የሚያሰችልም ስምምነት ትናንት በአክሱም ከተማ ተካሂዷል።

ሐወልቱን ለማደስም ሁለት ሚሊዮን ዩሮ የተመደበለት ሲሆን እድሳቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል ነው የተባለው ።

የትግራይ ማዕከላዊ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሚኪኤለ አብርሃ ፤ የአካባቢው ህብረተሰብ ለዓመታት ሐውልቱን የማደስ ጥያቄ ማቅረቡንና  ስራው ጥንቃቄን የሚፈልግ በመሆኑ ጥናት ሲደረግበት መቆየቱን አስረድተዋል ።

የሐውልቱ እድሳት የሚያከናወነው ኤም ኤች ኢንጂነሪንግ በተባለ አገር በቀል ድርጅት እና ከጣሊያን የተመለሰውን ሐውልት የዳግም ተከላ ስራ ባከናወነው  ስቱዲዮ ክሮቺ በተባለ የጣሊያን አማካሪ ድርጅት ነው።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ እና የአካባቢው ማህበረሰብ የሃውልቱን እድሳት ከሚያከናውኑት ድርጅቶች ጋር እንደሚተባበሩም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ዶክተር ጁሲፒ ኮፕላን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ታሪካዊ ቅርሶችን ለማደስ በሚያከናውናቸው ሥራዎች አገራቸው የሙያ እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያና ጣሊያን "የበርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት ናችው" ያሉት አምባሳደሩ፤ ይህም የሁለቱን አገሮች የእርስ በእርስ ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው አስረድተዋል።

አክሱም ሐውልት ከ1ሺ 700 ዓመት በላይ እድሜ ያለው ሲሆን፤ 160 ቶን ይመዝናል። ሐውልቱ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት እ.ኤ.አ በ1980 ተመዝግቧል-(ኢዜአ) ።