የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚስተር ፍሊፖ ግራንዲ ኢትዮጵያ የጎረቤት አገር ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ረገድ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ አደነቁ ።
ኮሚሽነሩ በዛሬው ዕለት 17ኛው የዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀንን በማስመልከት በጉኑል የስደተኞች መጠሊያ ካምፕ ባደረጉት ጉብኝት እንደገለጹት “ ኢትዮጵያ ለስደተኞች በሯን ክፍት በማድረግ ምሳሌ የምትሆን አገር ናት ” ።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ኢትዮጵያ የጎረቤት አገር ስደተኞችን ከማስተናገድ በተጨማሪ ሥልጠናና ትምህርት እንዲያገኙ በማስቻል ስደተኞች የወደፊት ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ እገዛ እያደረገች ነው ።
ኮሚሽነሩ በዛሬው ዕለት የዓለም የስደተኞች ቀንን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር መላው የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች ለስደተኞችን ለአስፈላጊው እርዳታ ምላሽ እንዲሠጡ ጥሪ አቅርበዋል ።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በደቡብ ሱዳን ያጋጠመውን ፖለቲካዊና ሰብዓዊ ቀውስ መፍትሄ እንዲያገኝም መሥራት እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል ።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም ለጎረቤት አገራት ስደተኞች በሯን ክፍት ማድረጓን ይገልጿል ።
የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ ልምድ በመውሰድ በመላው ዓለም የሚገኙ ስደተኞችን ለመደገፍ እጅ ለእጅ በመያያዝ የስደተኞችን አሰቃቂ ህይወት መታደግ ይገባዋል ብለዋል ።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እያሳደረች ያላው ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ እያደገ በመምጣቱ 17ኛውን የዓለም የስደተኞችን ቀን እንድታዘጋጅ ያስቻላት መሆኑን ተናግረዋል ።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ 850 ሺህ የሚሆኑ የሱዳን ፣ የደቡብ ሱዳን ፣ የሶማሊያና የኤርትራ ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች ።
በመላው ዓለም 65 ሚሊየን ህዝብ በተለያዩ አገራት በስደት የሚገኝ ሲሆን 1 በመቶ የሚሆኑ ብቻ ወደ ትውልድ አገራቸውና መንደራቸው ይመለሳሉ ።