የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር  ወደ ሙሉ ትግበራ መሸጋገሩ ተገለጸ

 የከተሞች የምግብ ዋስትና ኘሮግራም ወደ ሙሉ ትግበራ መሸጋገሩን የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ ።

የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኝነት ባለሙያዎች በስትራተጂው አፈፃፀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በፍጥነት እንዲታረሙ ለማድረግ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።

የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ  ለሚዲያና የህዝብ ግንኝነት ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ በተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዓውደ ጥናት ላይ እንደገለፁት  በከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በሶስት ክፍሎች ለይቶ ተጠቃሚ የሚያደርገው ይኸው ኘሮግራም ወደ ሙሉ ትግበራ ተሸጋግሯል ።

በሶስት ዓመታት ውስጥ 604 ሺህ የድሃ ድሃ ዜጎችን ተጠቃሚ ለሚያደርገው ለዚሁ ኘሮግራም 450 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተመድቦለታል፡፡

ዘንድሮ 190 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሰመራ በስተቀር አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ጨምሮ በ10 ከተሞች  ወደ ሙሉ ትግበራ ተሸጋግሯል ።

ከኘሮጀክቱ ተጠቃሚዎች መካከል 84 በመቶ የሚሆኑት በከተሞች ልማት ላይ በማሳተፍ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡

ተጠቃሚዎቹ በልማት ተሳትፈው ከሚያገኙት ገቢ 20 በመቶ እንዲቆጥቡና መንግስት ደግሞ 40 በመቶ እንዲቆጥብላቸው በማድረግ ከሶስት ዓመት በኋላ በኢኮኖሚ ራሳቸውን ችለው ወደ መደበኛ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል ።

''16 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ መስራት የማይችሉና ጧሪ የሌላቸው አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞች ፣ የጎዳና  ተዳዳሪ ህፃናትና በልመና ተዳዳሪዎች ሲሆኑ በየወሩ  ቀጥተኛ ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው'' ብለዋል።

በ11 ከተሞች በሙከራ ደረጃ የተጀመረው የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራም በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ወደ 972 ከተሞች በማስፋት 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎችን የቀን ገቢ ከ2 ዶላር በላይ ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል ።

የኤጀንሲው  የምግብ ዋስትና ዘርፍ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አሰፋ ፕሮግራሙ በአጀማመሩ አልዘገየም ወይ ? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው  ''ስራው በአፍሪካም ሆነ በአገሪቱ አዲስ በመሆኑና ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ በየደረጃው  የሰለጠኑ አመራሮች ከቦታቸው በመነሳታቸው ምክንያት አደረጃጀቱን በአዲስ መልክ ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የተወሰነ  ዘግይቷል'' ብለዋል፡፡

አሁን ግን ወደ ሙሉ ትግበራ ተገብቶ በደሴ ከተማ  ወርሃዊ ክፍያ የተፈፀመ ሲሆን  በሀዋሳ ፣ በድሬዳዋና በመቀሌም በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ለመክፈል ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል።

የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኝነት ባለሙያዎች በስትራተጂው አፈፃፀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በፍጥነት እንዲታረሙ ለማድረግ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።

በአገሪቱ በሚገኙ 972 ከተሞች  20 ሚሊዮን ህዝብ ይኖራል ተብሎ የሚገመት ሲሆን 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ መሆናቸው የኤጀንሲው መረጃ ይጠቁማል -(ኢዜአ)፡፡