ኢጋድ ብዝሃሕይወትን መጠበቅ የሚያስችል መተዳደሪያ ደንብ አጸደቀ

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ የቀጣናውን ብዝሃሕይወት በጋራ መጠበቅ የሚያስችል መተዳደሪያ ደንብ አጸደቀ።

የኢጋድ አባል አገራት የአከባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች በቀጣናው የብዝሃሕይወት ጥበቃና እንክብካቤ ላይ ባለፉት ሦስት ቀናት በአዲስአበባ በተወካዮቻቸው አማካኝነት የመተዳደሪያ ደንቡን ካፀደቁ በኋላ ጉባዔውን አጠናቀዋል፡፡

መተዳደሪያ ደንቡን ያፀደቁት ከጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ኡጋንዳ የተውጣጡ ሚንሰትሮች መሆናቸውን ነው የተመለከተው ፡፡

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ማህቡብ ማሊም በአባል አገራቱ የጸደቀው የመተዳደሪያ ደንብ የቀጣናውን ብዝሃሕይወት በአግባቡ ለማስተዳደር፣ ዘላቂ ልማትን ዕውን ለማድረግና የቀጠናውን የአኗኗር ሁኔታ ለማሻሻል የሚኖረውን ጉልህ ሚና ተሳቢ በማድረግ አባል አገራቱ የመተዳደሪያ ደንቡን በተግባር ለመተርጎም ሊተጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ፡፡

አገራቱ በተናጠል ብዝሃሕይወትን ለመጠበቅ የሚያከናዉኑትን ሥራ ከቀጣናው አገራት ጋር በማስተሳሰር የተቀናጀ ስትራቴጂካዊ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙት ብዝሃይወት ለቀጣናው ህዝቦች የሚፈለገውን ጥቅም አንዲሰጡ ለማድረግ የደንቡ ሚና የጎላ መሆኑንም ዋና ጸኃፊው አስረድተዋል ።

ደንቡ ኢጋድ ድንበር ዘለል ብሎ ካወጣቸው መርኃ ግብሮች መካከል የሚጠቀስ መሆኑንና አፍሪካ በ2063 አጀንዳዎችን እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የዘላቂ የልማት ግቦችን ዕውን ለማድረግ እንደሚያግዝም ዋና ፀሐፊው አብራርተዋል፡፡  

የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ በበኩላቸው፤ ደንቡ የአከባቢውን ብዝሃሕይወት ለመጠበቅ ወሳኝ ነው ብለዋል። 

ቀጠናው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥርና ሰፊ የብዝሃሕይወት ሐብት ያለበት በመሆኑ እነዚህን አጣጥሞ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ ብዝሃሕይወትን የማስተዳደር ልምድ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ለማጋራት እንዲሁም ከሌሎችም ትምህርት በመቅሰም የተሻለ የብዝሃሕይወት እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሏን አስተዋፅኦ ለመወጣት እንደምትተጋ አረጋግጠዋል፡፡

እንደዋልታ ዘገባ የመተዳደሪያ ደንቡ ኢጋድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያወጣውን ፖሊሲ ከግምት ያስገባ እንደሆነም በመድረኩ ተመልክቷል፡፡