የግብፅ ኮፕቲክ ክርስቲያኖች በዓላትን ከቤተ እምነታቸው ውጪ እንዳያከብሩ የሃይማኖት አባቶች አስጠነጠቀቁ

የግብፅ ኮፕቲክ ክርስቲያኖች በደህንነት ስጋት ምክንያት በዓላትን ከቤተ እምነታቸው ውጪ እንዳያከብሩ እና ሃይማኖታዊ ጉዞዎችን እንዳያካሂዱ የሃይማኖት አባቶች አስጠቅቀዋል ፡፡

ሰላማቸው እየታመሰ ካሉ ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ጎረቤት ሃገር ግብፅ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአሸባሪዎች ሰለባ እየሆነች መጥታለች፡፡

በቅርቡ እንኳን ሚያዚያ አንድ በተከበረው የሆሳዕና በዓል ላይ በሃገሪቱ ሁለት አብያተ ክርስትያናት ላይ በተፈፀሙ የሽብር ጥቃቶች 44 የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ህይወት አልፏል፡፡

በተመሳሳይ ግንቦት ወር ላይ ወደ ገዳም ጉዞ ሲያደርጉ በነበሩ የኮፕቲክ ክርስቲያኖች ላይ አይ ኤስ በፈፀመው የሽብር ጥቃት የ29 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ 

ሮይተርስ ያወጣው አዲስ መረጃ ደግሞ ጥቃቶቹን ተከትሎ የሃገሪቱ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በደህንነት ስጋት ምክንያት በዓላትን ከቤተ እምነታቸው ውጭ እንዳያከብሩ፣ ከቤተ እምነት ውጪ የሚከበሩ በዓላትን እንዲሰርዙና ሃይማኖታዊ ጉዞዎችን እንዳያከናውኑ የሃይማኖት አባቶች አስጠንቅቀዋል፡፡

ጉዞ ላይ ያሉ ምዕመናንም ጉዞአቸውን አሳጥረው እንዲመለሱ የቤተ ክርስትያኗ ጳጳሳት አሳስበዋል፡፡

ይህው የመረጃው ባለቤት ሮይተርስ የግብፅ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም የሃገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ያወጣውን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ እንዲሆን ማሳሰቧን የቤተ ክርስትያኒቱን ቃል አቀባይ አቡነ ራፊቅ ግሪሽን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ሰሞኑን የቤተክርስቲያኒቱ መግቢያዎች በበርካታ የደህንነት ሰዎች እየተጠበቀ እንደሆነ ያስነበበው ዘገባው ከታህሳስ ወር ጀምሮ በተደጋጋሚ የአይ ኤስ የሽብር ጥቃት 100 የኮፕቲክ አማኞች ህይወት አልፏል፡፡

ግብፅ ይህንን ተከትሎ ያወጀቺው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጇን ብታራዝምም  ዛሬ 5 ፖሊሶቿ  መገደላቸውን ነው የተገለጸው ፡፡