በትግራይ ከተሞች የመሬትና የይዞታ ማረጋገጫ ምዝገባ በአዲስ መልክ ሊካሄድ ነው

በትግራይ ክልል 12 ትላልቅ ከተሞች በፕሮጀክት ደረጃ ሲካሄድ የቆየው የከተሞች የመሬትና የይዞታ ማረጋገጫ ምዝገባ በአዲስ መልክ በኤጀንሲ ደረጃ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉ ተጠቆመ።

ምዝገባውን በኤጀንሲ ደረጃ ማካሄድ ያስፈለገው በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት እንዲያስችል ታስቦ ነው።

በትግራይ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አታክልቲ ገብረሕይወት እንደገለጹት፣ አዲሱ የኤጀንሲ አደረጃጀት ከከተማ መሬት ጋር በተያያዘ የተሟላና በቴክኖሎጂ የተደገፈ መረጃ እንዲኖር ያስችላል።

በዚህም መሬት አልምቶ የሚያቀርብ፣ ምዝገባ የሚያካሂድ፣ ዝውውር የሚፈጽምና ዋስትና የሚሰጥ አንዲሁም ከብድር ጋር በተያያዘና በተለያዩ ምክንያቶች እግድ የሚሰጥና የሚያነሳ አካል ተለያይቶ እንዲደራጅ መደረጉን ነው ያስታወቁት ።

"አዲሱ የኤጀንሲ አደረጃጀት በዘርፉ ፈጠን አገልግሎት ለመስጠትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ይፈታል" ብለዋል

እንዲሁም በከተሞቹ ውስጥ ያሉትን መሬቶችና የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በዝርዝር በመመዝገብ ኢንቨስትመንትን እንደሚያበረታታ አስረድተዋል

በካርታ የተደገፈ የተሟላ መረጃ መዝግቦ ለመያዝ የሚያስችል በመሆኑም በግለሰቦች የመሬት ይዞታ ላይ ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱት ክርክሮችን ለማስወገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የሚመዘገበው የባለቤትነት ይዞታ በማዘጋጃ ቤት ብቻ  ሳይወሰን በተለያዩ አካላት የሚቀመጥ በመሆኑ መረጃው የሚጠፋበት እድል ጠባብ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አቶ አታክልቲ  አንዳሉት፣ አዲሱን አደረጃጀት ከፊታችን መስከረም ወር ጀምሮ በመቐለ ከተማ "ዓዲሓቂ እና ሓድነት" ክፍለ ከተሞች በሙከራ ደረጃ ለማስጀመር የሰው ኃይልና ለስራው የሚያስፈልግ  ቴክኖሎጂዎችን የማሟላት ሥራ እየተከናወነ ነው።

በክልሉ 12 ትላልቅ ከተሞች ለስድስት ዓመታት በፕሮጀክት ደረጃ ሲካሄድ የቆየው የከተሞች መሬትና የይዞታ ማረጋጋጫ ምዝገባ አሰራር የሚጠበቀውን ያክል ተጨባጭ ለውጥ  አለማምጣቱም ተመልክቷል።

በቀድሞ የፕሮጀክት አደረጃጀት ከሚነሱ ችግሮች መካከል በደላሎችና በማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች ትብብር የሚፈፀም የፋይል መጥፋት ተጠቃሽ መሆኑን አቶ አታክለቲ አስታውቀዋል

ፕሮጀክቱ ሲቋቋም የህግ ማዕቀፍና ራሱን የቻለ አደረጃጀት ያልነበረው መሆኑ እንዲሁም በበቂ ባለሙያና  በቴክኖሎጂ  አለመደገፉ የሚጠበቀው ውጤት እንዳይመጣ ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል

"በዚህም ከከተማ መሬት ይዞታ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን መፍታት ሳይቻል ቆይቷል " ብለዋል( ኢዜአ )