የኬንያ እናቶች በምስራቅ አፍሪካ አነስተኛ የወሊድ መጠን እንዳላቸው ተመለከተ

ኬንያዊያን እናቶች በአማካይ አራት ልጆችን በመውለድ ከሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት እናቶች ያነሰ የወሊድ ምጣኔ እንዳላቸው ተጠቆመ፡፡

ኬንያዊያን እናቶች ጥቂት ልጆችን በመውለድ ሀገራቸው በምስራቅ አፍሪካ ዝቅተኛ የቤተሰብ አባላት ካሏቸው ሃገራት መካከል ቁጥር አንድ እንደትሆን አስችለዋል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ የቡሩንዲና ኡጋንዳ እናቶች  በርካታ ልጆችን በመውለድ ከዚሁ ቀጠና ተጠቃሽ ሃገራት ናቸው፡፡

ሰሞኑን ይፋ በሆነው መረጃ መሰረት ኬንያዊያን እናቶች ባለፉት ሁለት ተከታታይ አመታት በአማካይ 3 ነጥብ 9 የወሊድ ምጣኔ ሲኖራቸው፥ ይህም በፈረንጆቹ 2008 ከነበረው የ5 ነጥብ 0 ምጣኔ ያነሰ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ይህ የኬንያዊያን እናቶች የወሊድ ምጣኔ የአፍሪካዊያን እናቶች አማካይ የወሊድ ምጣኔ ሆኖ ከተመዘገበው 4 ነጥብ 6 ያነሰ ቢሆንም ከአለም አቀፉ የወሊድ ምጣኔ ግን የበለጠ ነው፡፡

በአለም አቀፉ መስፈርት መሰረት የአንድ እናት አማካይ የወሊድ ምጣኔ 2 ነጥብ 5 መሆኑንም መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የህዝብ ብዛት መረጃ ቢሮ አመልክቷል፡፡

በዚሁ መረጃ መሰረት ቡሩንዲያዊያን እናቶች በአማካይ ስድስት ልጆችን የሚወልዱ ሲሆን፥ ኡጋንዳዊያን እንስቶች በአንፃሩ 5 ነጥብ 4 ልጆችን በመውለድ ከቡሩንዲ ሴቶች በመቀጠል በርካታ ልጆችን ይወልዳሉ ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያዊያን እንስቶች 4 ነጥብ 6 ልጆችን እንደሚወልዱ መረጃው የጠቆመ ሲሆን፥ ታንዛኒያዊያን ደግሞ 5 ነጥብ 2 ልጆች በአማካይ ይኖራቸዋልም ብሏል፡፡

ለኬንያዊያን ሴቶች የወሊድ ምጣኔ አነስተኛ መሆን በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ኬንያዊያን እንስቶች እናት ለመሆን  ያላቸው ፍላጎት ቀዝቃዛ መሆኑና የወሊድ መከላከያ መድሃኒቶችን አብዘተው መጠቀማችውን በዋናነት መጠቀሳቸውን ያነሳል መረጃው፡፡

እኤአ በ1978 ላይ የኬንያ ሴቶች በአማካይ 8 ነጥብ 1 ልጆችን በመውለድ ስማቸው ይነሳ የነበረ ሲሆን አሁን የተመዘገበው 3 ነጥብ 9 የወሊድ ምጣኔ ግን በሃገሪቱ ከፍተኛ የግንዛቤ ለውጥ እንደመጣ ያሳያል ነው የተባለው፡፡

በቀጣቹ ሶስት አስርት አመታት ዉስጥም ይህን አሃዝ ወደ 2 ነጥብ 4 ዝቅ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ከሃገሪቱ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ( ምንጭ: ኢስት አፍሪካ)