የህፃናትን የንባብ ባህል ለማሳደግ በትኩረት እንዲሰራ ተጠየቀ

የህጻናትን የማንበብ ባህል በማሳደግ ብቁ አገር ተረካቢ እንዲሆኑ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ።

 'መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው' በሚል መሪ ሀሳብ ከነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በልዩ ሁኔታ እየተከበረ ያለው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ትናንት የንባብ ቀን ሆኖ ተከብሯል።

 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ዕለቱን አስመልክቶ  በብሔራዊ ቤተ መንግስት ለተገኙ ህፃናት የስነ ዜጋ ትምህርት አጋዥ መጽሀፍትን በስጦታ ያበረከቱ ሲሆን፤ ከመጽሃፉ ውስጥም ሁለት አንቀጾችን አንብበውላቸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ህጻናት በአእምሯቸው ጎልብተው ነገን በበቂ ሁኔታ ሊረከቡ የሚችሉት ዛሬ ላይ የማንበብ ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግ ሲቻል ነው።

 ይህ እውን ይሆን ዘንድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ገልጸዋል።

 "ለአገራችሁ የምትጠቅሙ ዜጋ እንድትሆኑ ዛሬ  በዋናነት የምትሰሩት ስራ ማንበብ ብቻ መሆን አለበት" ሲሉም ህጻናቱን መክረዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው ብቁ ዜጋ ለመፍጠር የተዘረጉት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች አንባቢ ትውልድ መፍጠር ካልተቻለ ውጤታማ ሊሆኑ  እንደማይችሉ ተናግረዋል።

 ሚኒስትሩ የህጻናትን የማንበብ ባህል በዋናነት ማዳበር የሚቻለው በትምህርት ቤት እንደሆነ ገልጸው፤ "መንግስት በትምህርት ቤት ውስጥ ባሉ  ቤተ መጻህፍት የመጽሃፍ ግብኣትን ለማሟላት በትኩረት እየሰራ ነው" ብለዋል።

 በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አማካኝነት በሁሉም የአገሪቷ ወረዳዎች የንባብ ማዕከላት እንዲኖር እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

 በልዩ ሁኔታ በሚከበረው በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የንባብ ቀን እንዲካተት መደረጉ መንግስት ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት እንደሚያሳይም ጨምረው  ገልፀዋል።(ኢዜአ)