የብሪክስ አባል አገራት መሪዎች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ ተስማሙ

የብሪክስ አባል ሃገራት መሪዎች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሰሚነታቸውን ከፍ እንዲል ለመስራት ተስማሙ ፡፡

በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ የመሠረቱት ማህበር በምህፃር ስሙ ብሪክስ 9ኛ መደበኛ ጉባኤው በቻይና ዢያሚን ከተማ ተካሂዷል፡፡

በጉባኤው ላይ የአባል ሃገራቱን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርና ማህበሩ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያለውን ተሰሚነት ለማሳደግ የአገራቱ  መሪዎች በመስማማት ነው ጉባኤያቸውን ያጠናቀቁት፡፡

የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ጂምፒንግ ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር የአባል ሃገራቱን የጋራ ትብብር የበለጠ በማጠናከር ለዓለም ሃገራትም ሰላምና እድገት መስራት አለብን ብለዋል፡፡

የብሪክስ አባል ሃገራት መሪዎች የሰሜን ኮሪያን የሀይድሮጅን ቦምብ ሙከራ ያወገዙ ሲሆን የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን ለማርገብ መፍትሄው በሰላማዊ መንገድ መወያየት ብቻ  መሆኑን አስምረውበታል።

መሪዎቹ በሌሎች የዓለም ሃገራት ወቅታዊ ሁኔታ ላይም የመከሩ ሲሆን የመካከለኛው ምስራቅ ሰላምን ለማረጋገጥ መስራት እንዳለባቸው አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡ በተለይም የእስራኤል እና ፍልስጤም የዘመናት ግጭትን በውይይት ለመፍታት ጥረታቸውን ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን መሪዎቹ መክረዋል።

የሶሪያ ቀውስን በማባባስ የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የመከሩት የብሪክስ አባል ሃገራት መሪዎች ዋናው መፍትሄ ግን ራሳቸው ሶሪያውያን በመሆናቸው ለዚህ መፍትሄና እርስ በእርስ ግጭቱ መቋጫ እንዲያገኝ አባል ሃገራቱ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

በተለይም በጉባኤው የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂምፒንግና የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በሁለቱ ሃገራት መካከል ሲያወዛግብ የነበረውን የድንበር ችግር በመፍታት መልካም ወዳጅነትን ለመመስረት መስማማታቸው ጉባኤውን  ስኬታማ እንዲሆን አድርጎታል  ።

የቻይና እና የህንድ ወታደሮች በዶክላም የድንበር አካባቢ ሲያደርጉት የነበረው ፍጥጫ ባለፈው ሳምንት ህንድ ወታደራዊ ኃይሏን ከዶክላም የድንበር አካባቢ ማንሳቷን ተከትሎ በሀገራቱ መካከል የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ውጥረት እንዲረግብ ማድረጉ ይታወቃል።

መሪዎቹ ሁለቱ ሃገራት በሂማሊያ ድንበር ላይ በፈጠሩት ውዝግብ ሳቢያ ላለፉት አስርት ዓመታት የዘለቀው ወታደራዊ ሽኩቻ ከተፈታ ወዲህ ሲገናኙ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

አሁን መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል  የሚታዩትን የድንበር ይገባኛል ጥያቄና አለመግባባቶችን በማስወገድ የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ጤናማና የተረጋጋ ግንኙነት እንዲኖር  ነው የተስማሙት፡፡

ቤጂንግ በህንድ ውቅያኖስና በአካባቢው ያላት ወታደራዊ እንቅስቃሴ በኒው ደልሂ አይወደድም።

በሌላ በኩል ቻይና ቲቤትን እንደግዛት የምትቆጥራት ሲሆን ኒው ዴልሂ ቲቤት የቻይና ግዛት አይደለችም ብለው ከሚቃወሙት ወገኖች ጋር ትቀራረባለች በሚል ቤጂንግ ትወቅሳለች፡፡ እናም የአሁኑ የመሪዎቹ ስምምነት ይህን ችግር ይፈታ ይሆን የሚለው ጥያቄ መፍጠሩ አልቀረም፡፡

ሲጂቲኤን እንደዘገበው ከሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ብሪክስ በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን በማመን ለማህበሩ ድጋፉ እንዳለው አረጋግጧል።(ምንጭ:ሲጂቲኤን)