ቢቢሲ በኢትዮጵያና ኤርትራ በሶስት ቋንቋዎች ስርጭት ጀመረ

ቢቢሲ በኢትዮጵያና ኤርትራ በአማርኛ ኦሮሚኛና ትግርኛ የዜናና የተለያዩ ፕሮግራሞች ሥርጭት እንደጀመረ በይፋ አስታወቀ፡፡

እ.ኤ.አ ከ1940ዎቹ ጀምሮ አገልግሎት ላይ የሚገኘዉ አንጋፋዉ የእንግሊዝ ዜና ማሰራጫ ተቋም የስርጭት አገልግሎቱን በኢንተርኔትና በፌስቡክ ዜናዎችን በማቅረብ የሚጀምር ሲሆን በመቀጠልም የ15 ደቂቃ የዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም የ5 ደቂቃ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት ፕሮግራም በአጭር የሬድዮ ሞገድ እንደሚጀምር አመልክቷል፡፡

አዲሱ አገልግሎትም ሚዛናዊ የሆኑ ዜናዎችን በሁለቱ አገራት ከማቅረብ በተጨማሪ በአካባቢዉም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚሰጡ ዝግጅቶች እንደሚኖሩትም ጠቁሟል፡፡

አዲሱ አግልግሎት ሌላዉ አለም ኢትዮጵያና ኤርትራን በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረዉ የሚያደርግ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ወጣቱን ትዉልድ ይበልጥ ኢላማ አድርጎ እንደሚሰራ የገለፀዉ ጣቢያዉ ከዜና በተጨማሪ ባህል መዝናኛ የስራ እድል ፈጠራ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጤናና ስፖርትን የተመለከቱ ፕሮግራሞች እንደሚኖሩት ለማወቅ ተችሏል፡፡