የሩዋንዳው ባንክ ኦፍ ኪጋሊ በምርጥ አገልግሎት አለም አቀፍ ሽልማት አገኘ

የሩዋንዳው ባንክ ኦፍ ኪጋሊ ምርጥ አገልገሎት በመሥጠት የአለም አቀፍ ሽልማት አገኘ።  

50ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ ያከበረው ባንክ ኦፍ ኪጋሊ ይህን ሽልማት ያገኘው ለ5ኛ ጊዜ መሆኑም ታወቋል፡፡

በሩዋንዳ ቁጥር አንድ የሆነው ባንክ ኦፍ ኪጋሊ እኤአ በ2017 ላይ በተረገው የምርጥ ባንኮች ውድድር በምስራቅ አፍሪካ ሪጂን ከሚገኙ ባንኮች የተሻለ በሚል ነው ሽልማቱን ያገኘው፡፡

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የአገልግሎት ልምድ ያለው ይህ ባንክ እኤአ ከ2009 ወዲህ ብቻ ይህንን ሽልማት ሲያገኝ ለአምስተኛ ጊዜ እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡

ባንክ ፍ ኪጋሊ በአፍሪካን ባንከርስ አዋርድ አዘጋጅነት የሚደረገውን ይህን ውድድር በተደጋጋሚ ማሸነፉን ተከትሎ  መልካም ዝናን ማትረፍ በመቻሉ የሩዋንዳዊያን ቀዳሚ ምርጫ እንደሆነም ዘገባው አያይዞ ገልጿል፡፡

የባንክ ኦፍ ኪጋሊ ዋና ስራ አስኪያጅ ዲያኔ ካሩሲሲ ሽልማቱን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ባንኩ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና በሚሰጠው በዚህ ውድድር አሸናፊ በመሆኑ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል፡፡

ለተመዘገበው ውጤት ሁሉም የባንኩ ሰራተኞችና አመራሮች የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባልም ብለዋል ዲያኔ፡፡

በቀጣይም ባንኩ አዳዲስና ዘመናዊ የፋይናንስ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የቀዳሚነት ሥፍራ ለማስጠበቅ አንደሚሰራም ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ ሪጂን በሚገኙ ባንኮች መካከል በተደረገው በዚህ ምርጫ የኡጋንዳው ስታንቢክ ባንክ፣ የኬንያው ህብረት ሥራ ባንክ፣ የታንዛኒያው ሲ አር ዲ ቢ ባንክና የቡሩንዲው ኢኮ ባንክ ከባንክ ፍ ኪጋሊ ጋር እስከ መጨረሻው ድረስ መፎካከር የቻሉ ባንኮች ናቸው፡፡

ባለፈው ዓመት የአመቱ ምርጥ ኩባንያ የሚል ስያሜን ከኦል አፍሪካን ቢዝነስ ያገኘው ባንኩ ከዩሮ መኒ እና ፋይናንሻል ታይምስም ተመሳሳይ ክብርም ተሠጥቶታል፡፡

የባንኩ አመራሮች ቁርጠኝነት እንዲሁም እጅግ የሠለጠነ የሪፖርቲንግ ሲስተም ባንኩን ባለፉት ቅርብ ዓመታት ውስጥ ላስመዘገበው ውጤት አብቅተውታልም ነው የተባለው፡፡

አንደ ዲያኔ ገለጻ ባንኩ የደምበኞቹን እርካታ ጠብቆ መዝለቅ መቻሉ እና ከባለአክሲዮኖች ጋር በቅርበት መስራቱ ላስመዘገባቸው ስኬቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡( ምንጭ: የዘ ኒው ታይምስ)