ዘንድሮ በስድስት የአርብቶ አደር ክልሎች ከ48ሺህ በላይ ቤተሰቦችን በመንደር በማሰባሰብ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ ።
በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ወርቁ ለዋልታ እንደገለጹት በተያዘው የበጀት ዓመት በአፋር ፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ ፣ ደቡብ ፣ ቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎች አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚገኙ 48ሺህ39 ቤተሰቦችን በአዳዲስ የመንደር ማሰባሰቢያ ማዕከላት በማሰባሰብ የተለያዩ መሠረታዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ይገኛል ።
ሚኒስቴሩ ባወጣው ዕቅድ መሠረት በሶማሌ ክልል 15ሺህ ፣ በአፋር 15ሺህ ፣ በኦሮሚያ 4ሺህ ፣ በደቡብ 9ሺህ 410 ፣ በጋምቤላ 3ሺህ 886 እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ 743 የሚሆኑ ቤተሰቦችን ወደ አዳዲስ መንደሮች ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን አቶ አበበ ጠቁመዋል ።
በስድስቱም ክልሎች ተግባራዊ በሚደረገው የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም በአጠቃላይ 441 የሚደርሱ የተለያዩ መሠረታዊ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተገንብተው ለአርብቶ አደሩ አገልግሎት መሥጠት እንደሚጀምሩ አቶ አበበ አመልክተዋል ።
በክልሎቹ የሚካሄደው የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ስኬታማ እንዲሆን ለማድረግ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከወዲሁ ከፌደራል ፣ ከክልል ፣ ከዞን ፣ ወረዳ ፣ የቀበሌ አመራሮችና ከአርብቶ አደሩ ጋር ግንዛቤ የመፍጠርና የማግባባት ሥራዎች እንደሚካሄዱ አቶ አበበ አስገንዝበዋል ።
የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስቴር በነደፈው የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም በአጠቃላይ 365ሺህ 909 የሚደርሱ የአርብቶ አደር ቤተሰቦችን በመንደር ማዕከላት በማሰባሰብ ሙሉ ለሙሉ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ የማድረግ ዕቅድ አለው ።