የኡጋንዳ ፓርላማ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ የእድሜ ጣራ እንዲነሳ የሚፈቅደውን አዋጅ አፀደቀ

የሀገሪቱ ገዥው ፓርቲ ለፓርላማው ያቀረበው ረቂቅ አዋጁ ለፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ለስድስተኛ ጊዜ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ እድል የሰጠ ነው ተብሏል።

የፕሬዚዳታዊ ምርጫ እጩ እድሜ ምን ያህል መሆን እንዳለበት ለመወሰን የተሰባሰቡት የፓርላማ አባላት ለሁለት ተከታታይ ቀናት ያደረጉት ስብሰባ ፈር የለቀቀና አባላቱ በቁሳቁስ ሳይቀር እንዲደባደቡ ምክንያት እንደነበር ነው የአልጀዚራ ዘገባ ያመለከተው፡፡

የኡጋንዳ ህገመንግስት ለፕሬዚዳንት የሚወዳደር እጩ እድሜው የግዴታ ከ75 ዓመት በታች መሆን እንዳለበት ይደንግጋል።

 የፕሬዚዳንታዊ እጩ የእድሜ ጣራን ለማንሳት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ውሳኔ ለማሳለፍ የተሰበሰቡት የገዥው የናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት ፓርቲ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎችም ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥረዋል ነው የተባለው።

ማክሰኞ እለት በነበረው የምክር ቤቱ ስብሰባ በተፈጠረ ረብሻ እና ድብድብ ምክንያት የሀገሪቱ አፌ ጉባኤ ርብቃ ካዳጋ 25 የምክር ቤቱ አባላት በፀጥታ ሃይሎች ከስብሰባው እንዲወጡ አድርገዋል ።

የተቃዋሚ ፓርቲው “ፎረም ፎር ዴሞክራቲክ ቼንጅ” መሪ ዊኒ ኪዛ ከስብሰባው መውጣታቸውን ተከትሎ፥ ውዝግብ እና ረብሻ ያስተናገደው ፓርላማው የፕሬዚዳንታዊ እጩ የእድሜ ጣራ እንዲነሳ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡