የወላይታ-ሶዶ ዩኒቨርስቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 3ሺህ 105 አዳዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ከወዲሁ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን አስታወቀ ።
የወላይታ- ሶዶ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ዶክተር ሰንበቴ ቶማ ለዋሚኮ እንደገለጹት በ2010 የትምህርት ዘመን ዩኒቨርስቲው 3ሺህ 105 የሚሆኑ አዳዲስ ተማሪዎችን በመቀበል በ50 የትምህርት ዘርፎች ለማስተማር ተዘጋጅቷል ።
እንደ ዶክተር ሰንበቴ ገለጻ ዩኒቨርሰቲው አዳዲስ ተማሪዎችን ጥቅምት 6 እና 7 2010 ዓም በሦስቱ ካምፓሶች ለማስገባት አስፈላጊ መሰናዶዎችን በሙሉ አጠናቋል ።
የወላይታ -ሶዶ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ቅበላ አቅሙን ለማሳደግ ትምህርት ሚኒስቴር በመደበለት የ470 ሚሊዮን ብር በጀት የመማሪያ ክፍሎች ፣ የመሠረተ ልማትና የቢሮዎች ግንባታን እያከናወነ ይገኛል ።
ዩኒቨርሰቲው የማስፋፈያ ግንባታዎች ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቀም በአጠቃላይ ተማሪዎች የማስተናገድ አቅሙን 17ሺህ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ዶክተር ሰንበቴ አመልክተዋል ።
የወላይታ -ሶዶ ዩኒቨርስቲ በ2009 የትምህርት ዘመን 2ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን በ50 የትምህርት ዘርፎች ማስመረቁ ይታወሳል ።