ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከል መንግስት ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን እንዲወጣ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ጥሪ አረበ፡፡

የጤና ጥበቃ ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ በዓለም ለ30ኛ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ በአማራ ክልል በኮምበልቻ ከተማ እየተከበረ ባለው የፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ ቀን በዓል ላይ መንግስት እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ጉዳዩ አሁን ካለበት አሳሳቢ ደረጃ አንጻር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሚዲያ አካላት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ድርጅቶች ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቫይረሱ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደ አዲስ መስፋፋት መጀመሩን የገለጹት ዶክተር ከበደ፥ መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል ከዚህ በፊት ከሰጠው ትኩርት በተሻለ መልኩ እንደሚሰራም አስታውቀዋል። ለማሳያነትም በባህርዳር እና በኮምቦልቻ ከተሞች ከሚኖሩ ሴተኛ አዳሪዎች በቅደም ተከለተል 32 እና 29 በመቶ ያህሉ በደማቸው የኤችአይቪ ቫይረስ እንደተገኘባቸው ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ700ሺ በላይ ዜጎች የኤችአይቪ/ኤድስ ቫይረስ በደማቸው እንደሚገኝና ከ27ሺ በላይ ዜጎች ደግሞ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ዜጎች በመሆናቸው አሃዙ የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት በሀገሪቱ የኤችአይቪ/ኤድስ ወረርሽኝ ሊባል በሚችል ደረጃ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡

የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭት ፍጥነት በዚህ መልኩ ከቀጠለ ከ10 ዓመታት በኋላ በፊት ወደ ነበረበት አስከፊ ሁኔታ ሊመለስ እደሚችልም በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ19 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ አማካኝነት ይሞታሉ፡፡

በየዓመቱ ህዳር 22 የሚከበረው የፀረ ኤችአይቪ ቀን በዓል "አሁንም ትኩረት ለኤችአይቪ/ ኤድስን ለመከላከል!" በሚል መሪ ቃል እየተከበረ መሆኑን ዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዘግቧል፡፡