ሰሜን ኮሪያ ጠላቶቿን ማጥቃት የሚያስችል ሚሳኤልን በማምረት ለሙከራ ማብቃቷን አስታወቀች

ሰሜን ኮርያ ባላንጣዎቼ የምትላቸውን አካላት አነጣጥሮ ሊመታ የሚችል ሚሳኤል በማምረት ሙከራ ማድረጓን አስታወቀች፡፡

ሰሜን ኮርያ አሁን ይፋ ባደረገችው መረጃ እስካሁን ድረስ ካደረገቻቸው የበለጠ ከፍተኛ ኃይል ያላቸው 15 የባላስቲክ ሚሳኤሎችን ማምረቷን አስታወቀች ፡፡

ቢቢሲ ባስነበበው መረጃ ሀገሪቷ ያደረገችው አዲስ የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራ የተሳካ ነበር፡፡ አህጉር አቋራጩ የባላስቲክ ሚሳኤል የአሜሪካንን የትኛውንም ግዛት መምታት ይችላል ነው የተባለው፡፡

የሰሜን ኮሪያ የዜና አውታርን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው ፒዮንግያንግ ያደረገችው አዲሱ የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራ በ4ሺ475 ኪሎሜትር ከፍታ በ53 ደቂቃ ከ950 ኪሎሜትር በላይ ተጉዞ ማረፉ ተጠቅሷል፡፡

የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራው ለአሜሪካና ጃፓን ማስጠንቀቂያ መስጠትን ያለመ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ሚሳኤሉ ከ13 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በላይ መጓዝ የሚችል ሲሆን እስካሁንም ከተደረጉት ሙከራዎች እጅግ በጣም የላቀ ነው ተብሏል፡፡

በጀፓን ግዛት በቅርብ ርቀት ላይ የተደረገው የሚሳኤል ሙከራ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባዘዙትም መሰረት የተተገበረ ነው፡፡ በዚህ ሙከራና ሀገራቸው በደረሰችበት የኒውክለር ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ኩራት እንደሚሰማቸው መናገራቸዉን ነው ቢቢሲ በዘገባው ያወሳው፡፡

የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራው በዓለም ታሪክ የመጀመሪያ ነው ያሉት ኪም ዮንግ ኡን ይህ ስኬት የሮኬት ኃይል ያላቸውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለመገንባት ሌላ መንገድ እንደሚጠርግላቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አሉ ኪም ዮንግ ኡን አሜሪካ ከራሷ ውጭ ሌላው የኒውክለር ባለቤት እንዳይሆን ያስቀመጠቸው ፖሊሲ የተሳሳተ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ማለታቸዉን ዘገባው ያመለክታል፡፡

እኛ የኒውክለር ባለቤት እና ሰላም ወዳድ ሀገር እንደመሆናችን መጠን ሰሜን ኮሪያ ለዓለም ሰላም እና መረጋጋት አስፈላጊዉን ሁሉ ታደርጋለች ማለታቸው ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ የአሜሪካ ዛቻና ማስፈራሪያ ከአላማቸው እንደማያስቆማቸውም ገልጣል፡፡

በሌላ በኩል ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን የሰሜን ኮሪያን የባላስቲክ ሙከራን የነቀፉ ሲሆን አሜሪካ እና ጃፓን ሰሜን ኮሪያን ለመከላከል በጋራ መስራት እንዳለባቸው አስታውቋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የጦር ኃይላቸዉን ለማጠናከር አዲስ ስምምነት አድርገዋል፡፡ ቻይና በሃገራቱ መካከል የተፈጠረዉን ውጥረት ለማርገብ መሥራት እንደምትፈልግ እየገለፀች ትገኛለች፡፡

በተለያዩ ወቅት የተራቀቁ የኒውክሌር ሙከራዎችን ያደረገችው ሰሜን ኮሪያ አሁንም ከድርጊቷ ከመታቀብ ይልቅ የዓለም ስጋትና ፀብ አጫሪነት ድርጊቷ ቀጥላለች የሚሉም አልጠፉም፡፡