በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ4ሺ 300 በላይ ዜጎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን እንደሚነጠቁ ተገለጸ

በኢትዮጵያ  በየዓመቱ  ከ4ሺ 300 በላይ ዜጎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ገነቱ ደሳለኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ12ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ የተከበረውን የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች የመታሰቢያ ቀን  አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር በዓለማችን በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 25 ሚሊየን በላይ ዜጎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን እንደሚያጡና የክስተቱ 90 በመቶ የሚሆኑት ተጎጂዎች ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

አቶ ገነቱ የዓለም ዓቀፉን የጤና ድርጅት መረጃ ጠቅሰው እንደገለጹት በትራፊክ አደጋ የሚሞቱት ከ15 አስከ 29 ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ክስተቱ የሀገሮችን አምራች የሰው ኃይል በመንጠቅ ከድህንት ለመውጣት በሚያድርጉት ጥረት ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡

ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ የደህንነት ሕጎችን መጣስና ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት ለአደጋው መባባስ ዋንኛ ምክንያቶች መሆናቸውን በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለስልጣን አደጋውን ለመቀነስ የመንገድ ደህንንት ካውንስል በማቋቋምና ስትራቴጂ በማውጣት ወደ ትግበራ በመግባት ላይ እንደሆነ ገልጾ፣ ከትራፊክ አደጋ ነፃ የሆነ እንቅስቃሴን እውን ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንዲሰሩበት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡