የመቅደላ አምባ ዩኒቨርስቲ ተመርቋል

በደቡብ ወሎ  ዞን  አካባቢ  በ457  ሚሊዮን  ብር ግንባታው የተከናወነው የመቅደላ አምባ ዩኒቨርስቲ  በይፋ  ተመርቋል

በመቅደላ ዩኒቨርስቲ የመርቃ ሥነ ሥርዓት  ላይ  የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ  መኮንን ፣የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ  ፣ የአማራ ክልል ክልል ርዕሰ መስተዳድር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፣ የትምህርት ሚንስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴና ሌሎች  ከፍተኛ የመንግሥት  የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል ።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን  እንደገለጹት  ዩኒቨርስቲው ከመላ አገሪቱ  የተውጣጡ   ተማሪዎች እውቀት የሚገበዩበትና በታሪክና ትውፊት የሚታነፁበትና ብሔራዊ አንድነትን ግንባታን የሚያጠናክሩበት   እንደሚሆን እተማመናለው ብለዋል ።    

የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው በአገሪቱ የትምህርት ፍትሃዊነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ   ዘርፈ ብዙ ሥራዎች  እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው  የመቅደላ አምባ ዩኒቨርስቲ  ለአካባቢው ማህበረሰብ  የሚጠቅሙ ጥናቶችና ምርምሮች ን  በማድረግ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚኖርበት አመልክተዋል ።

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት የሆኑት ዶክተር ታምሬ ዘውዴ የዩኒቨርስቲው መሠረት ድንጋይ በ2007 ዓም መጣሉን ጠቁመው በመጀመሪያው ዙር ግንባታን  በማጠናቀቅ  በመካነ ሰላምና ጋምቢ ካምፓሶቹ አገልግሎት መጀመሩን ይፋ አድርጓል ።

በመቅደላ  አምባ ዩኒቨርስቲ ከመማሪያ ፣ የተማሪዎች ማደሪያና የተለያዩ  ቢሮዎች   ህንጻዎች ግንባታ በተጨማሪ  በ570 ሚሊዮን ብር የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለሟሟላት የተለያዩ  የግንባታ ሥራዎች በአካባቢው እየተካሄዱ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ወቅት  በአጠቃላይ  1ሺህ 135 ተማሪዎችን  ተቀብሎ   በሚቀጥለው ሳምንት የመማር ማስተማር ሥራውን ለማስጀምር  እየተዘጋጀ መሆኑን  ዶክተር  ታምሬ ተናግረዋል ።

በዘንድሮ ዓመት  ወደ ሥራ  ከሚገቡት  አዳዲስ  ዩኒቨርስቲዎች  መካከል  የመቅደላ  አምባ ዩኒቨርስቲ   አንዱ መሆኑ ዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት ዘግቧል ።