የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን የዘጠኝ ወር አፈጻጻም ገመገመ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ  ኮሚቴ ትናንት ባደረገው  ስብሰባ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጻም ሪፖርትን  ገመገመ ።

በባለሥልጣኑ የአየር ትራንስፖርትና ዕቅድ ዳይሬክተር አቶ እንደሻው ይገዙ የባለሥልጣኑን የዘጠኝ ወራት አፈጻጻም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት መሥሪያ ቤቱ በዘጠኝ ወራት  ውስጥ ያከናወናቸውን ሥራዎችና ያጋጠሙትን ችግሮች ለኮሚቴው አቅርቧል ።

አቶ እንደሻው በሪፖርታቸው  ባለሥልጣኑ አዋጆችን በማሻሻልና በማጽደቅ፣ በሰው ኃይል ልማት ፣ የህግ ማስከበርና ከሠራተኞች  ጋር ተግባብቶ በመሥራትና ከአየር መንገዱ ጋር ተግባብቶ በመሥራት ረገድ ችግሮች እንዳሉበት ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል ።

የምክር ቤቱ የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው ባለሥልጣኑ እስካሁን ድረስ የመልካም  አስተዳደር  ማነቆዎች ለምን አልተፈቱም በሚል ጥያቄዎችን አንስተዋል ።

የቋሚ ኮሚቴ አባላት ላነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሠጡት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን  ዋና  ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ  ሁነኛው በበኩላቸው መሥሪያ ቤቱ እንደሌሎች ተቋማት ሁሉ በአሠራር ሂደት የሚያጋጥሙት ችግሮች  እንዳሉ ጠቁመው  የመልካም አስተዳደር ችግሩን  ለመፍታት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል ።

በተጨማሪም ሚያዚያ 9 ፣ 2010 ዓም የተፈጠረውን የአየር በረራ መስተጓጎልን በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ የቀረበላቸው የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የተወሰኑ የአየር በረራ ባለሙያዎች ፍቃድ በመውሰዳቸው አንድ ሠራተኛ ቦታውን ሸፍኖ ለመሥራት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የተከሰተ  ችግር መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል።

ባለፈው ማክስኞች ዕለት የተፈጠረውን የአየር መስተጓጎል ችግርም ከአየር ትራፊክ ቁጥጥር ኃላፊው ጋር  በተደረ ውይይት በአፋጣኝ መፍታት መቻሉን  ኮሎኔል ወሰንየሌህ አያይዘው ገልጸዋል ።

በመጨረሻም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን   ያሉበትን  ችግሮች በመቅረፈ ረገድ ጠንክሮ  እንዲሠራም አሳስበዋል ።