ሮቤና ጊኒርን የሚያገናኘው የጮሪኖ ድልድይ በመደርመሱ በአካባቢው ያለው እንቅስቃሴ መቋረጡን ነዋሪዎች ገለጹ

በሮቤ ጊኒር አብይ መንገድ ላይ የሚገኘው የጮሪኖ ድልድይ በመደርመሱ በአካባቢው ያለው እንቅስቃሴ መቋረጡን ነዋሪዎች ለዋልታ ቴሌቪዥን ገለጹ፡፡

ይህ አብይ መንገድ የባሌ ዞን መዲና የሆነችውን የሮቤ ከተማ  ከዞኑ ቆላማ አካባቢዎች እንዲሁም በምርታማነታቸው ከሚታወቁት እንደነ ጊኒር፣ ጎሎልቻና አጋርፋ ከመሳሰሉ አካባቢዎች የሚያገናኝ ብቸኛ መንገድ ነውም ተብሏል፡፡

ይህ መንገድ በዞኑ የሚገኙ ሰባት ወረዳዎችን ከማስተሳሰሩም በላይ የኦሮሚያ ክልልን በጎዴ በኩል ከሶማሌ ክልል ጋር እንደሚያገናኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡

መጋቢት 27 ቀን 2010 ላይ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ድልድዩ በመደርመሱ ሙሉ በሙሉ ከአገልግሎት ውጪ ሲሆን አፋጣኝ መፍትሄ ባለመሰጠቱ ለተጨማሪ ወጪና እንግልት መዳረጋቸውን ነዋሪዎቹ ለዋልታ ገልጸዋል፡፡