የክልሉ መንግስት ባለፉት ሶስት ዓመታት ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ሊያደርግ መሆኑን ገለጸ

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባለፉት ሶስት ዓመታት በክልሉ ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ሊያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን በሰጡት መግለጫ የክልሉ መንግስት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አጋርነቱን በማሳየት ዘመዶቻቸው ለሞቱባቸው ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው 75 ሺህ ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ደግሞ 50 ሺህ ብር እንደሚሰጥ ነው ያስታወቁት።

ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ዜጎች ደግሞ የጉዳቱን መጠን የሚያጠና ቡድን ጥናት እያካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ ንጉሱ የአጥኚው ቡድን በደረሰበት ድምዳሜ መሠረት የሚከፈላቸው ይሆናል ብለዋል።

ከስራቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ደግሞ ከአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም የተበደሩት ብድር ካለ የመክፈያው ጊዜ እንዲራዘምላቸው የክልሉ መንግስት መወሰኑን አቶ ንጉሱ በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል።

የአማራ ክልል መንግስት መሰል ችግሮች እንዳይደርሱ ከአጎራባች ክልሎች ጋር እና ከህብረተሰቡ ጋር ምክክር የማድረግ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ (አማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት)