የአገር ፍቅርና የአንድነት አስተሳሰቦችን በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ የሚያስችሉ ተግባራት ለመከወን የቤት ሥራ መውሰዳቸውን የኪነ– ጥበብ ሙያተኞች ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ከኪነ–ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን የአገር አንድነትን እና አብሮነትን ለማጉላት ጥረት እያደረጉ ለሚገኙት የኪነ–ጥበብ ሰዎች ያላቸውን አክብሮት በውይይቱ ላይ ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የኪነ–ጥበብ ባለሙያዎች እንደተናገሩት በውይይቱ ላይ የተነሱ ሀሳቦች የኪነ–ጥበብ ሙያተኞች ለአገር ሰላምና ዕድገት መጫወት የሚጠበቅባቸውን ሚና ለማጎልበት የሚያግዝ ነው።
አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ ውይይቱ ስኬታማና የተነሱ ሃሳቦችም የኪነ–ጥበብ ባለሙያዎች በተሰማሩበት ዘርፍ ያላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያጎለብቱ የሚያግዝ ነው ብሏል።
የኪነ–ጥበብ ባለሙያው በማንኛውም አገራዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ዙሪያ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ አጋዥ ሀሳቦችን ለማመንጨት አቅም ያለው መሆኑ የተብራራበት እንደሆነም ገልጿል።
“ዘርፉ በተለይም ይቅርታንና ስነ–ምግባርን በተመለከተ የህብረተሰቡን አመለካከት ለመግራት ትልቅ መሳሪያ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩት መሰረት ሙያተኛው የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ ነው” ሲል አርቲስት ደሳለኝ ተናግሯል።
በውይይቱ የኪነ–ጥበብ ሙያተኛው የአገራዊ አንድነትንና መደመርን የሚሰብኩ ሥራዎችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ አገሪቱን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የበኩሉን እንዲወጣ የቤት ሥራ የተጠሰው መሆኑንም አክሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ስራ አስኪያጅ አርቲስት ነብዩ ባዬ በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ለህዝበ እየቀረቡ ባሉት የፊልምና ቴአትር ሥራዎች ኢትዮጵያ ከመግለጽ አኳያ ክፍተት እንዳለባቸው በውይይቱ መነሳቱን ጠቁሟል።
ውይይቱ የኪነ–ጥበብ ዘርፉ “የኢትዮጵያዊነት” ትክክለኛ ገፅታና ስሜትን ከመግለጽ አኳያ ወደፊት በስፋት ሊሰሩ በሚገባቸው ቁም ነገሮች ላይ ትኩረት የተሰጠበትና ሙያተኛውም በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታዎች እንዲኖሩ ዕድል የፈጠረ ነው ሲልም ተናግሯል።
“በአጠቃላይ ውይይቱ የኪነ–ጥበብ ሥራዎች የህዝቡን ችግር በማንሳት መፍትሄ እንዲመጣና ያልታዩ ጉዳዮችን በመዳሰስ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ለመጀመር ስንቅ ሆኖናል” በማለት ነው አርቲስት ነብዩ የገለፀው።
‘በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማረጋጋት የኪነ–ጥበብ ባለሙያው የሚጠበቅበትን ሚና አለመጫወቱ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል’ የሚል ሀሳብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መነሳቱን የገለጸው ደግሞ ገጣሚ ታገል ሰይፉ ነው።
የኪነ–ጥበብ ባለሙያው እነዚህን በመሳሰሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በድፍረት በመስራት ስሜቱን መግለጽ እንደሚችል መገለጹን የተናገረው ታገል ሰይፉ በዚያው ልክ የአንድነትንና አብሮነት አስተሳሰቦችንም ለማጎልበት መትጋት እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቶታል ብሏል።
“ትውልዱን በተሟላ ስብእና ለመቅረጽ ከወላጆች በተሻለ የኪነ–ጥበብ ባለሙያው መዋእለ – ህጻናት ድረስ በመውረድ ጭምር በሙያው ትውልዱን ሊያንጽ ይገባል በተባለው መሰረትም የድርሻችንን እንወጣለን ብለን ተግባብተናል” ብሏል።
የፊልምና የቴአትር ባለሙያው አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በበኩሉ መጤ ባህልን ከማስቀረት አኳያ በተለይም ወጣቱ አገር ወዳድና ለአገሩ ተቆርቋሪ እንዲሆን የኪነ–ጥበብ ባለሙያው የድርሻውን መወጣት ላይ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባ በውይይቱ መነሳቱን ጠቁሟል።
የቀድሞ የኪነ–ጥበብ ባለሙያዎች ያበረከቷቸው ሥራዎች አሁንም የሚወሱ በመሆናቸው የአሁኑ ትውልድና የዘርፉ ባለሙያዎችም የቆዩትን አርአያ በመከተል የማይረሱ ስራዎችን ማበርከት እንደሚገባ ከመድረኩ መነሳቱን አውስቷል።
ውይይቱ ኪነ–ጥበብ በሁሉም ዘርፍ ገንቢ ሚና መጫወት የሚችል አቅም ያለው መሆኑ የተወሳበት መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
ባለሙያውም ያለበትን ክፍተት እንዲያይም አድርጎታል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኪነ–ጥበብ ባለሙያዎችን ሰብስበው ማነጋገራቸው ሁሉም ሙያተኛ የቤት ስራን እንዲወስድና በተግባርም እንዲወጣ ያነሳሳው መሆኑንም ነው ሙያተኞቹ የገለፁት።(ኢዜአ)