የአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አዲሱን የትምህርት ዘመን በመልካም መንፈስ እንዲጀምሩ ዝግጅት አድርጓል

የአዳማ ዩኒቨርስቲ በአጠቃላይ  ተማሪዎች የዘመኑን ትምህርት  በመልካም  መንፈስ  እንዲጀምሩ የሚያስችል   ደማቅ የአቀባበል መርሃ ግብር  ማዘጋጀቱን አስታወቀ ።  

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ የዘመኑን ትምህርት በመልካም መንፈስ እንዲጀምሩ  የአቀባበል መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል።

ባለፉት ሦስት ወራት የተማሪዎች የምግብ፣ የመኝታ፣ የጤና፣ የቤተ መጻህፍትና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችንም አሟልቷል።

ሠላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት ዘንድሮ በተሳካ ሁኔታ እንደሚካሄድ እምነታቸውን ገልጸዋል። 

ተማሪዎቹ የአዳማ ከተማ ማህበረሰብን ችግሮችን የሚፈቱበት ዕቅድ ማዘጋጀቱንና ከተማሪዎች ጋር በሚደረገው ውይይት መግባባት ላይ ሲደረስበት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገባል ብለዋል።

በያዝነው የትምህርት ዘመን የዩኒቨርሲቲው የመግቢያ ፈተና ከወሰዱት 4 ሺህ 500 ተማሪዎች ውስጥ ፈተናውን ያለፉት አንድ ሺህ 500 ተማሪዎችን መቀበሉን ዶክተር ለሚ ተናግረዋል።

ከነዚህም 1 ሺህ 300 የሚሆኑት የምህንድስና ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ናቹራል አፕላይድ ሳይንስ ተማሪዎች ናቸው።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ ዩኒቨርሲቲው 8 ሺህ አዲስና ነባር ተማሪዎችን ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ባሉት መርሐ ግብሮቹ ለማስተማር ዝግጅት አጠናቋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ እንዲሪስ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ምርጥ ሳይንቲስት ሆነው በመውጣት ለአገራቸውና ለወገናቸው ኩራት እንዲሆኑ አሳስበዋቸዋል።

ተማሪ ሳሌም ግርማ በሠጠችው አስተያየት የአቀባበል ሥነ ሥርዓት መማረኳን ገልፃ፣ በቆይታዋ ከስሜታዊነት በመራቅና በምክንያታዊነት የመጣችለትን ዓላማ ለማሳካት እንደምትተጋ ገልጸለች።

ሌላው የአንደኛ ዓመት ተማሪ ጌሹ ፍቅረማርያም በበኩሉ ዩኒቨርሲቲው አዲስ አበባ ድረስ ትራንስፖርት በመመደብ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልፆ፣ ቆይታው ከማንኛውም አሉታዊ እንቅስቃሴ ነፃ በመሆን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀቱን ይናገራል።