የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጥገና ለማስጀመር 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተገኘ

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን በሚካሄደው የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማግኘቱን የክልሉ ባህል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክተል ኃላፊ አቶ ልኡል ዮሐንስ እንደገለጹት የላሊበላ አለም አቀፍ ቅርስ ከተደቀነበት የመፍረስ አደጋ ለመታደግ ስራዎች ተጀምረዋል።

የቅርሱን ጥገና ለመጀመር ቀደም ሲል የጉዳት መጠን ልየታና እንዴት ሊጠገን ይችላል የሚል የጥናት ሰነድ በባለሙያዎች ተዘጋጅቷል፡፡

ለጥገናውም 300 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም መታወቁን ገልፀዋል።

ለቅርሱ ዘላቂ ጥገና ለማስጀመር የአማራ ክልል መስተዳደር ምክር ቤት 30 ሚሊዮን ብር ለዚህ ዓመት የመደበ ሲሆን የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ደግሞ 20 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ”በተገኘው ገንዘብ በዘርፉ ልምድ ያላቸውን አለም አቀፍ ተቋራጮች በማሳተፍ የተሰራውን ከዝናብና ፀሐይ መከላከያ መጠለያ ማንሳትን ጨምሮ ሌሎች የቅርስ ጥገና ስራዎች ይጀመራሉ” ሲሉ አቶ ልኡል አስታውቀዋል።

”ላሊበላ በገንዘብ የሚገመት ቅርስ አይደለም” ያሉት ምክትል ቢሮ ሃላፊው የክልሉ መንግስት በቀጣይም አስፈላጊውን በጀት ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

”የፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትም ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።

በተለይም የቅርሱ ዋናው ባለቤት የሆነው መላው ህዝብ በገንዘብ፣ በሞራልና በእውቀት ቀደም ሲል የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አንዳለበትም አሳስበዋል።

የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በተባበሩት መንግስትት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኒስኮ በአለም አቀፍ ቅርስ የተመዘገበ መሆኑ ይታወሳል። (ኢዜአ)