የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከመስከረም ወር ጀምሮ የካንሰር ህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታወቀ

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከመስከረም 2፤2011 ጀምሮ የካንሰር ህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ሆስፒታሉ ህክምናውን ከጀመረበት ቀን አንስቶ ከ300 በላይ የካንሰር ታማሚዎችን በተመላላሽ ማከሙንም ገልጿል፡፡

በሆስፒታሉ የካንሰር ህክምና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አብዲ አደም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይህንን ህክምና መጀመሩ ከዚህ በፊት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በቦታ ጥበት ምክንያት በወረፋ  ለሚንገላቱ ታካሚዎች መፍትሔ ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

እስካሁን በተመላላሽ ህክምና ለታካሚዎች አገልግሎት ሲሠጥ መቆየቱን የገለጹት ዶክተር አብዲ በቅርቡ አስተኝቶ ማከም የሚያስችል ወደ 350 የሚጠጋ አልጋ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ዋልታ ያነጋገራቸው በሆስፒታሉ የካንሰር ታካሚዎች እንደገለጹት ከዚህ በፊት ህክምናውን ለማግኘት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እስከ ስድስት ወር እንደሚወስድ ገልጸው አሁን ግን በቅዱስ ጳውሎስ  አገልግሎት መጀመሩ ያለምንም ወረፋ ህክምናን ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተደራጀ የጥናት ውጤት ባይኖርም በግምት በዓመት ከ160 ሺህ በላይ የካንሰር ተጠቂዎች እንደሚኖሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት ለአንድ ሚሊዮን ሰዎች አንድ የካንሰር ህክምና ተቋም ሊኖር እንደሚገባ ቢመክርም በኢትዮጵያ ግን ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በብቸኝነት የህክምናው አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡