የወጪ ንግዱ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ ሀብት የሚያሳይ ባለመሆኑ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለፀ

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ ሀብት የሚያሳይ ባለመሆኑ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ተግዳሮቶች ዙሪያ ያተኮረ ውይይት እና የንግድ ትርዒት በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ በዛሬው እለት መካሄድ ጀምሯል፡፡

የውይይት መድረኩ የአምራች ዘርፉንና ፋይናንስ ዘርፉን ማቀራረብ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ አፈጻጻም በተከታታይ ወደ ታች መውረዱና በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን አስመልክቶ በርካታ ምክንያቶች በውይይቱ ተጠቅሰዋል፡፡

የገበያ መዋዠቅ እና ለዘርፉ የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እንደ ችግር በዋናነት ተነስተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ ኢትዮጵያ ያላት እምቅ አቅምና አሁን እየታየ ያለው የወጪ ንግድ አፈጻጻም እኩል አለመሆኑን ገልጸው ሀገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያስችሉ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በርካታ ተግዳሮቶች የተጋረጡበት የወጪ ንግድ የፋይናንስ ዘርፍ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ማምጣት አለመቻሉን ያነሱት ዲኤታው ችግሩን ለመፍታት መሰራት እንዳለበት እና መንግስትም ትኩረት እንደሚሰጠው ነው የገለጹት፡፡

የፋይናንስ አቅርቦቱን መቅረፍ እንዲያስችል ባንኮች ድጋፍ በማድረግ አጋዥ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሀገሪቱ ወጪ ንግድ በግብርና ምርት ብቻ እንደተንጠለጠለና ይህንንም በተለያዩ ዘርፎች ማሳደግ ይገባዋል ያሉት አምባሳደር ምስጋናው ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ በዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዲቀረፉ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡

ውይይቱ ለሁለት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች በሳይንሳዊ መልኩ ተለይተው የመፍትሔ አቅጣጫ ሊሆኑ የሚችሉትን  ነጥቦች ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡