በሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚስተዋሉ መከፋፈሎችንና ልዩነቶችን ለማጥበብ የሚያስችል ረቂቅ ሰነድን በማጠናቀቅ በህዝብ ውይይት ለማድረግ መዘጋጀቱን የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አስታወቀ ።
ኮሚቴው በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በሠጠው መግለጫ ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያከናወናቸውን ተግባራት ዘርዝሯል ።
ኮሚቴው በመግለጫ የሙስሊሙን አንድነት ዳግም ለመመለስ የተወሰደው የቤት ሥራ ለመፈጸም ሰፊ ጊዜ መድቦ የተለያዩ ተግባራትን ሲፈጽም መቆየቱን አንስቷል ።
ኮሚቴው ከመሥረታው ጀምሮ የተሠጠውን ኃላፊነቱን ለመወጣት እንዲያግዘው እስካሁን የህግ ጉዳዮችን ፣ የመዋቅር ጥናት፣ የኡለማዎች መግባቢያ ሰነድ ዝግጅትና የገንዘብ አፈላላጊ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ሥራዎችን በሚገባ መወጣታቸው በመግለጫቸው ተመልክቷል ።
አሁን በተዘጋጀው የኡለማዎች የመግባቢያ ሰነድ መሠረት የመጅሊሱን ፣ የኡላማ ንክር ቤቱንና የአገሪቱን የአስልምና ምክር ቤት አዲስ አቅጣጫ በማመላከት አላስፈላጊ የጭቅጭቅ መድረኮችን የሚያስቀር መሆኑ ተገልጿል ።
በቅርቡ ኮሚቴው በተባበሩት የአረብ ኢምሬቶች የመጅሊሱን አወቃቀርና ሌሎች አሠራሮችን በተመለከተ ልምድ ቀስሞ መምጣቱም በመግለጫው ተጠቁሟል ።
በኮሚቴው የተዘጋጀው ሰነድ በመጪው ህዳር ወር በተመረጡ የክልል ከተሞችና ወረዳዎች ውይይት የሚደረግ መሆኑን ተገልጿል ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ባቀረቡት ምክር ሓሳብ መሠረት ዘጠኝ አባላት ያሉትን የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰኔ 26፤ 2010 ዓም መቋቋሙ ይታወሳል ።