የኦሮሞ አባገዳዎች በሶማሌላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ

ኦሮሞ አባገዳዎች በሶማሌላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም የኢትዮጵያና ከሶማሌላንድ ህዝቦች  የሚያስተሳስሯቸውን በርካታ ነገሮችን ለጋራ ተጠቃሚነት ለማዋል  በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ  ተወያይተዋል ።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የኦሮሞ አባገዳዎች አንድነት ሰብሳቢ አባገዳ በየነ ሰንበቶ እንደገለፁት በተለያዩ የስራ መስኮች ለተሰማሩ ኢትዮጵያዊያንና የሶማሌላንድ ዜጎች ሰላምና አንድነትን ማረጋገጥ ቁልፍ ተግባራት በመሆናቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል ።

በውይይቱ የተገኙት ኢትዮጵያውያንም የሁለቱ አገሮች በትብብር መሥራት የህገወጥ ንግድና የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚያደርጉትን  ጥረት  እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የኦሮሞ አባገዳዎች ከሶማሌላንድ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ከሆኑ የአገር ሽማግሌዎችና ሱልጣኖች ጋር ውይይት አካሂደዋል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችም መቀጠል ይገባዋል ሲሉ በውይይቱ ላይ አንስተዋል።

በቀጣይም የሶማሊላንድ የህዝብ ልዑካን  ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝና ተመሳሳይ ጉብኝት በማከናወን ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባ የአገር ሽማግሌዎቹ ጠቁመዋል።

በሶማሌላንድ ዋና ከተማ ሐርጌሣ የኢትዮጵያ ኮሌጆች፣ የሕክምና ተቋማት እና ሬስቶራንቶች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

በሶማሌላንድ ከ16 ሺህ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡