የፕላዝማ ማዕከልን በቴክኖሎጂ የማገዝና ወደ ዲጂታል ሲስተም የመቀየር ስራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የትምህርት ማሳራጫ (ፕላዝማ) ማዕከሉን በቴክኖሎጂ የማገዝና ወደ ዲጂታል ሲስተም የመቀየር ስራው ተጠናቆ አገልግሎት መሥጠት ጀመረ፡፡ 

የኢኖቬሽን አና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከደቡብ ኮርያው የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በ2016 በተፈራረመው የትብብር ስምምነት መሰረት የትምህርት ማሰራጫ ማዕከሉን ከአናሎጎ ወደ ዲጂታል ሲሰተም ለመቀየር የሚያስችለው ፕሮጀክት ዝርጋታ ሥራ ተጠናቆ ተመርቋል፡፡

የትምህርት ሥርዓቱን ለመደገፍ ከሚሰሩ ስራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የትምህርት ማሠራጫ ማዕከሉን ዲጂታላይዝ የማድረጉ ስራ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመራሮች፣ የኮሪያ የሬዲዮ ማስተዋወቂያ ማኅበር ምክትል ዳይሬክተር እና የኮርያ የሳይንስ እና አይ.ሲ.ቲ ሚኒስቴር ባለሙያዎች በተገኙበት ነው የተመረቀው፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ የፕሮጀክቱ አላማ የትምህርት ማሰራጫ ማዕከሉን ወደ ዲጂታል ሲስተም በመቀየር የትምህርት ስርዓቱን በዘመነ ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ፍትሀዊ እና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን በማስቻል በተመሳሳይ የትምህርት ስርዓትና እስታንዳርድ ሁሉንም የሀገሪቱን ተማሪዎች ማብቃት ነው ብለዋል፡፡

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የትምህርት ስርዓቱን ለማገዝ እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ በትምህርት ማህበረሰቡ ስም ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ሙሉ ወጭ በደቡብ ኮርያ መንግስት የተሸፈነ መሆኑም በምረቃው ወቅት ተገልጿል፡፡ (ምንጭ፡-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)