የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት ተከበረ

የጥምቀት በዓል በመላ አገሪቱ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሰቲያን ምዕመናን ዘንድ በድምቀት  ተከበረ።

በተለይም በዓሉ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ባህረ ጥምቀት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለ ኃይማኖትን ጨምሮ የተለያዩ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምዕመናንና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በተገኙበት ተከብሯል።

በዓሉ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማንያን በተጨማሪ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድም በድምቀት ተከብሯል።

በጃንሜዳ በተከናወነ ስነ ስርዓት ላይ ለምዕመናኑ የ2011ዓ.ም የጥምቀት በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ “እኛ ኢትዮጵያውያን የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ልንገለገልባቸው፤ አካባቢያዊ ክልሎችን ልንተዳደርባቸው እንጂ ልንጋጭባቸው አይገባም” ብለዋል።

መለያየት፣ ጠማማነትና የተመሰቃቀለ ማህበራዊ ህይወት ሀገራችንን ብሎም ዓለምን እየተፈታታነ እንደሆነ በመግለጽ፥ ሰው በመሆናችን ብቻ ተስማምተን፣ ተጋግዘን፣ ተዋደን፣ በአንድነትና በእኩልነት በመኖር ፋንታ በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋና በመልክዓ ምድር እየተከፋፈልን እርስ በርሳችን እንዳንጎዳዳ መጠንቀቅ ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ሰው ከሰው የበለጠ ማንነት እንደሌለው ለማስረዳት እግዚአብሄር ሁላችንም ሰው ተብለን እንድንጠራ አድርጓል ብለዋል።

በዛሬው እለት በመላ ሀገሪቱ የተከበረው በዓል ድምቀትም የኢትዮጵያውያን መተባበር፣ መከባበርና መደጋገፍ መሆኑን በመጠቆም ተለያይቶና ተጣልቶ ድምቀትም ውበትም የሌለ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ለዚህም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች በየአካባቢያቸው የሚሳሳቱን፥ በተለይም ወጣቶችን በመገሰፅና በመምከር ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ወጣቶችም የመደማመጥ፣ የመታዘዝና ርህራሄ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ መክረዋል።

ከትናንት የከተራ በዓል ጀመሮ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ቱሪስች በበዓሉ ላይ የታደሙ ሲሆን፥ ተመሳሳይ በዓል በተለያዩ ሀገራት የሚከበር ቢሆንም የኢትዮጵያዊያንን ያህል ትኩረት የሚስብ የሌለ መሆኑን ቱሪስቶች ተናግረዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የኢትዮጵያን አለባበስ፣ ጭፈራና ለእምነታቸው የሚሰጡት ትኩትረት የቱሪስቶችን ቀልብ መሳቡን ጎብኚዎቹ ይነገራሉ።

ከትናንት የከተራ በዓል ጀምሮ የታደሙት ቱሪስቶቹ ኢትዮጵያ ይህንን ስርዓት በመጠበቅና በመንከባከብ ለዓለም ማስተዋወቅ እንዳለባት አሳስበዋል።

የተለያዩ የሀገሪቱን የቱሪስት መስህብ ቦታዎች የመጎብኘት እቅድ ያላቸው ቱሪስቶቹ ከትናንት የከተራ በዓል ጀምሮ ይሁንኑ ጉብኝታቸውን በደስታ መጀመራቸውንም ነው የተናገሩት።

በዓሉ ከአዲስ አበባ ውጪ የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ በርካታ ምዕመናንና ምዕመናት እንዲሁም፥ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በተገኙበት በጎንደር፣ ላሊበላ፣ አክሱምና በሌሎች አካባቢዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትተከታዮች፣ አድባራትና ገዳማት በድምቀት ተክብሯል።

የጥምቀትና የከተራ በዓላት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተካታዮች ዘንድ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊና የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ ነው። (ኤፍ.ቢ.ሲ)