የተፈናቀሉ ዜጎቻችን ሁሉም ወደነበሩበት ይመለሳሉ — የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት

በተለያዩ ጊዜያት ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ሁሉም ዜጎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደነበሩበት ቦታ እንደሚመለሱ አዲሱ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ተናገሩ።

በአምቦ ከተማ እየተካሄደ ባለው የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች የጋራ የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደተናገሩት  በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ነበሩበት አካባቢያቸው ይመለሳሉ ብለዋል፡፡

ዜጎችን በመመለስ ስራ ላይ ቀን ከሌት እንደሚሰሩ ያወሱት ምክትል ፕሬዘዳንቱ፤ “ከዚሁ ጎን ለጎን አፈናቃዮችን በመከታተል እርምጃ እንወስዳለን” ነው ያሉት፡፡

“አፈናቃነት ጠላታችን ነው ፣ ኋላ ቀርነትም ነው ፣ የተሸናፊዎች ተግባርም ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ከሶስት ሺህ ዘመን  በፊት ጀምሮ  የኦሮሞ ብሄረሰብ ለአፈናቃዮች ቦታ እንደሌለው ያስቀመጠውን ባህል የክልሉ መንግስትም ይህን ቱባ ባህል ወደተግባር እንደሚቀይረው ነው የተናገሩት፡፡

ማፈናቀል እንዳይኖርና የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው ከመመለሱ ጎን ለጎን ለኢትዮጵያ አንድነት ይበልጥ መጠናከር እንሰራለንም ብለዋል፡፡

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ በማጠናከር በአራቱም አቅጣጫ እንሰራለን ያሉት ፕሬዘዳንቱ፤ ፅንፈኞች ኖሩም አልኖሩም ሀገራችን ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

ሁሌም ለኢትዮጵያዊነት መስዋእትነት በሚከፍለው  የአምቦ ህዝብ መሃል ተገኝታችሁ ይህን ታሪካዊ ጉባዔ ማካሄዳችሁ ሊያኮራችሁ ይገባልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡/ኢዜአ