የብሄራዊ ዕርቅ ኮሚሽን አባላት በኬንያ ልምድ ልውውጥ ማድረግ ጀመሩ

የኢትዮጵያ የብሄራዊ ዕርቅ ኮሚሽን አባላት በኬንያ መዲና ናይሮቢ በመገኘት የልምድ ልውውጥ ማድረግ ጀምረዋል።

ዛሬ በይፋ በተከፈተው የልምድ ለውውጥ መድረክ አካል በሆነው ስልጠና ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ለታሳታፊዎቹ ኢትዮጵያውያን ከግጭት ይልቅ ለእርቅና ይቅርታ ባይነት መስራት ይገባናል ብለዋል።

ከጎረቤቶቻችን ተሞክሮዎችን መቅሰምና የመማር ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው፤ ለሀገራችን ኢትዮጵያም በጣም አስፈላጊ ነው ሲሉ አምባሳደር መለስ አክለዋል።

ቡድኑ በናይሮቢ ቆይታው በኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ የተካሄዱ የሃቅ እና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ትምህርት ለመቅሰም የሚያስችል የልምድ ልውውጥ ያደርጋል።

ከዚህም በተጨማሪ በኬንያ የብሄራዊ የአንድነት ኮሚሽን አስራር፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ለሰላም ግንባታ በሚኖራቸው ሚና ላይ ስልጠና ይወስዳሉ።

ጉብኝቱን በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው በሰላም ግንባታ ላይ የተሰማራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ያዘጋጁት ሲሆን እስከ 7 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።

(በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ)