የአፍሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አዲስ የመድሃኒት ስርጭት ስትራቴጂ አጸደቀ

አዲስ አበባነሐሴ 18/2008(ዋኢማ)-የአፍሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ የመድኃኒት ምርት በገበያ ላይ እንዲያሰራጭ የሚያስችል አዲስ ስትራቴጂ አፀደቀ።

ስትራቴጂው በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ ይደረጋልም ተብሏል።

አዲሱ ስትራቴጂ የአገራቱ ባለሥልጣናት ጥራቱና ደህንነቱ ያልተረጋገጠ መድኃኒት በገበያ ላይ እንዳይሰራጭ ህጋቸውን ጥብቅ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነው።

አገራቱ የመድኃኒት ጥራትን ማረጋገጥና መቆጣጠር የሚያስችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ላቦራቶሪ መገንባት እንደሚጠብቅባቸውም እንዲሁ።

በአፍሪካ በየቀኑ ጥራት የጎደለው፣ሐሰተኛና ደህንነቱ ያልተረጋገጠ መድኃኒት በገበያ ላይ ይሰራጫል፤በግልፅና በስፋት እንደሚቸበቸብም የመንግስታቱ ድርጅት  መረጃ ያመለክታል። 

ይህ ደህንነቱ ያልተረጋገጠ መድኃኒት  ደግሞ በዜጎች ላይ የጤና እክል ከመፍጠሩ በላይ ፋርማሲዎችንና ፋብሪካዎችን ለኪሳራ እየዳረገ ይገኛል።

በመንግስታቱ ድርጅት የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ማቲሺዲሶ ሞቲ እንዳሉት ስትራቴጂው የየአገራቱ  የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣናት አሰራራቸውን ጥብቅ እንዲያደርጉ ያስገድዳል።

ይሄው ስትራቴጂ በ66ኛው ዓመታዊ የአፍሪካ ጤና ጉባዔ በመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ ለውይይት ቀርቦ ፀድቋል።

እንደሳቸው ገለፃ ባለስልጣናቱ የመድኃኒት ጥራትን የሚያረጋግጡበት መሳሪያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆን ይኖርበታል።

ይህም የኅብረተሰቡን ጤና በሚገባ ከመጠበቅ ባለፈ የዓለም ጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ያስችላል ነው ያሉት።

በዓለም ጤና ድርጅት አባል ከሆኑ 47 የአፍሪካ አገራት መካከል የመድኃኒት ምርቶችን መቆጣጠር የሚያስችል ህግ ያላቸው 40 ሲሆኑ ቀሪዎቹ አገራት ግን ህገ ደንብ የላቸውም።

ከእነዚህ መካከልም 15  አገራት ወደ አገራቸው የሚገባውንና በገበያ ላይ የሚሰራጨውን የመድኃኒት ምርት ይቆጣጠራሉ።

ቀሪዎቹ ግን በአቅም፣በክህሎት፣በአቅርቦት፣በፋይናንስና በሰው ኃይል እጥረት ምክንያት ስራቸውን በሚገባ እየሰሩ አይደለም ተብሏል።(ኢዜአ)