ቫይታሚን D የአስም በሽታን ከመከላከል አንጻር ጠቀሜታው የጎላ ነው

የመተንፈሻ አካል እክል የሆነውን አስምን ለማከም በተለያዩ ጊዜያቶች የተለያዩ ጥናቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል አሁንም በመካሄድ ላይ ናቸው።

ታዲያ ከሰሞኑም “ቫይታሚን D” የአስም በሽታን ለመከላከል ይረዳል የሚለውን የጥናት ውጤት ይፋ ተደርጓል።

እንደ ተመራማሪዎቹ አነስተኛ መጠን ያለው የቫይታሚን D የሚወስዱ ሰዎች በቀላሉ ለአስም በሽታ የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ ነው ብለዋል።

ስለዚህ ይላሉ ተመራማሪዎች ቫይታሚን D’ን አዘውትረው የሚወስዱ ሰዎች ለአስም በሽታ ተጋላጭነታቸው አነስተኛ ነው።

ለአስም እንዳንጋለጥ ይረዳ ዘንድም በተለያየ መንገድ የምናገኘውን ቫይታሚን D መውሰድ ይመከራል ባይ ናቸው።

ጥናቱ በእንግሊዝ ለንደን ኩዊን ሜሪ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ ሲሆን፥ በዚህም 435 ህጻናት እና 658 አዋቂዎች ተሳታፊ ተደርገዋል።

በጥናቱም ቫይታሚን D አዘውትረው የሚወስዱ ሰዎች የአስም ተጋላጭነታቸው ከሌሎች አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን አረጋግጠናል ይላሉ ተመራማሪዎች።

በተለይም ቫይታሚን D አዋቂዎች በቀላሉ ለአስም በሽታ እንዳይጋለጡ በማድረገ ረገድ ከፍተኛ ሚና ነው የሚጫወተው የሚለውን አክለዋል።

የጥናት ቡድኑ መሪ ዶክተር አድሪያን ማርቴኒቱ፥ ይህ የጥናት ውጤት ቫይታሚን D የአስም ተጋላጭነትን ይቀንሳል እንጂ ይከላከላል የሚለው በጥናቱ ላይ አልተገለጸም ብለዋል።

ስለዚህ ይላሉ ዶክተሩ ቫይታሚን D የአስም በሽታን ሙሉ በሙሉ ስለማይከላከል የአስም በሽታ መድሃኒትን የሚወስዱ ሰዎች መድሃኒታቸውን ማቋረጥ የለባቸውም ብለዋል።

በቅርቡ የተሰራ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው በዓለማችን ላይ ከ300 ሚሊየን በላይ ሰዎች የአስም ችግር እንዳለባቸው ያሳያል።( ኤፍቢሲ)