የደቡብ አፍሪካ ምጣኔ ሃብት በዜሮ ነጥብ 7 በመቶ መቀነሱን የሃገሪቱ መንግስት ገለጸ

የደቡብ አፍሪካ ምጣኔ ሃብት በዜሮ ነጥብ 7 በመቶ ማሽቆልቆሉን የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ ።

እኤአ በ2017 የመጀመርያው ሩብ አመት ነው የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ በ0ነጥብ 7 በመቶ ቅናሽ ያሳየው ፡፡

ሀገሪቱ እኤአ በ2016 4ኛው ሩብ ዓመት ላይም የ0ነጥብ 3 በመቶ የኢኮኖሚ ቅናሽ ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡

እኤአ ከ1961 ወዲህ ብቻ ሃገሪቱ በ8 የተለያዩ ጊዜያት ተከታታይ የኢኮኖሚ ውድቀት አስመዝግባለች፡፡

በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ዉስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የንግድና ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ኢኮኖሚውን ለመታደግ  ጥረት ቢያድርጉም  የንግዱ ዘርፍ 5ነጥብ 9 በመቶ የማምረቻው ዘርፍ ደግሞ 3ነጥብ7 በመቶ  ቅናሽ ማስመዝገባቸው  አልቀረም፡፡

በተለይም የማምረቻ ዘርፉ ለ3ኛ ተከታታይ ሩብ አመት ማሽቆልቆሉም በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡

በሌላም በኩል በግብርናውና በማዕድን ልማቱ ዘርፍ እድገት መመዝገቡ በበጎ ጎኑ ቢጠቀስም የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ግን ከማሽቆልቆል ሊታደገው አልቻለም፡፡

በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ዘርፍ ላይ የተመዘገበው ውድቀትከ2009 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ  መሆኑም ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

የማዕድን ልማቱ ዘርፍ  የወርቅ፣ የከበሩ ድንጋዮችና የፕላቲኒየም ምርቶች መጠንን  ከፍ ማድረግ በመቻሉ የደቡብ አፍሪካ ምጣኔ ሃብት ከዚህም በከፋ መልኩ እንዳያሽቆለቁል ማስቻሉን  የሃገሪቱ መንግስት በሪፖርቱ ገልጿል፡፡