የዓለም ባንክ 1 መቶ ሺህ የሚጠጉ ጅቡቲያውያንን ተጠቃሚ የሚያድርግ ፈንድ ይፋ አደረገ

በጅቡቲ የሚገኙ በዝቅተኛ ገቢ ኑሯቸውን የሚመሩ 1 መቶ ሺ ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ የሚያስችል አዲስ ፈንድ በአለም ባንክ ይፋ ተደርጓል፡፡

የጅቡቲ መንግስት እኤአ በ2035 የፈረንጆቹ ዓመት ሁሉም የሀገሪቱን ዜጎች የኤልክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በዕቅድ አስቀምጧል ፡፡

አዲሱ የዓለም ባንክ ድጋፍም ይህንን የመንግስት ዕቅድ ግብ ይመታ ዘንድ ለመደገፍ ዓለማ ያለው እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡

በአዲሱ የዓለም ባንክ ፈንድ መሰረት አስራ አራት ሺህ እማውራና አባውራዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ ይህ ማለት ደግሞ መቶ ሺህ ዜጎች በፕሮጀክቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ነው ድርጅቱ ያስታወቀው፡፡

23 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተመደበለት አዲሱ የዓለም ባንክ ፕሮጀክት የመብራት መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ከዋና ከተማዋ ጅቡቲ ባሉ አጎራባች ከተሞችም የመንገድ ላይ መብራት ዝርጋት ፣ የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ተከላ እንዲሁም ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ነው ፡፡

ይህ ቀጣይነት ያለው የኤሌክትሪክ ኋይል አቅርቦት መርሃ ግብር በዓለም ባንክ እና በዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ደሃ ሀገራትን ለመደገፍ ከሚከናወነው ፈንድ ነው፡፡

ያሁኑ ፈንድም በተለይ በሀገሪቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉባትን የባልባላ አካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

በቀጣይም የሀገሪቱን ገጠራማ አካባቢዎች መካከለኛ የኃይል ፍሰት እንዲጠቀሙ ያደርጋል፡፡

ባለው መረጃ መሠረት አሁን ላይ ግማሽ ያህል ጅቡቲያውያን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ይህ ማለት በሀገሪቱ ሰባ ሺሀ ዜጎች መብራት ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ይሁን እንጅ የኃይል አቅርቦት እጥረት ፣ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ እንዲሁም የኃይል መቆራረጥ በአነስተኛ የቢዝነስ ዘርፍ የተሰማሩ የጅቡቲ ዜጎችንአሁንም ድረስ ይፈታተናል፡፡ 

አዲሱ የዓለም ባንክ ፕሮጀክትም የሀገሪቱ መንግስት እኤአ በ2035 የተያዘውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በመላ ሀገረቱ ተደራሽ ለማድረግ የተያዘውን እቅድ ይደግፋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የዓለም ባንክ  በጅቡቲ አስር ፕሮጀክቶች በተለያዩ ዘርፎች ያሉት ሲሆን አጠቃላይ 101 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ወጪ የሚካሄዱ ናቸው ፡፡