ጋቦን ከአይ ኤምኤፍ በምታገኘው ብድር የነዳጅ ጥገኝነቷን እንደምትቀንስ አስታወቀች

ጋቦን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ በሚሠጣት የ642 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር የነዳጅ ጥገኝነቷን በመቀነስ ሥራ ላይ እንደምታውልና  አስታወቀች፡፡

በቀን ከ200 ሺ በርሜል በላይ ነዳጅ የምታመርተው ጋቦን ከ30 በመቶው የሃገሪቷ አጠቃላይ ምጣኔ ሃብት  መሠረቱ ነዳጅ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠመው የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ምክንያት እንኳን በተለይም  እኤአ  በ2015 3ነጥብ 9 ነመቶ የነበረው የሃገሪቷ ምጣኔ ሃብት ዕድገት  በ2016 ወደ ሁለት ነጥብ አንድ መቀነሱን የብሉምበርግ ዘገባ ያሳያል፡፡

ሃገሪቷ በአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ ቃል የተገባላትን 642 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ስታገኝ የነዳጅ አቅርቦት መጠኗን በመቀነስ ፊቷን ወደ ግብርና እና የማዕድን ስራ እንደምታዞር የሃገሪቱ የምጣኔ ሃብት ሚኒስቴር ረጊስ ኢሞንጉልት ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት ከሆነ ጋቦን ብድሩን ስታገኝ አሁን ያለውን 30 በመቶ የነዳጅ ገቢዋን እኤአ በ2020 አጋማሽ ወደ 25 በመቶ ዝቅ ታደርገዋለች፡፡

ድጎማዎችን በመቀነስ እና የውጭ ኢንቨስተሮችን የሚያሳትፍ የንግድ ሁኔታን በመፍጠር, ምጣኔ ሃብታዊ እድገቷ ወደ 5 በመቶ ሊደርስ ይችላል ተብሏል ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እኤአ  ከ2013  በኋላ  የመጀመርያው ትልቁ ስኬቷ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ ) ብድሩን ያፀደቀው ባለፈው ሳምንት እንደሆነ ያወሳው የብሉምበርግ ዘገባ ጋቦን እኤአ  በ1995 ከነዳጅ አምራችና ላኪ ሃገራት ማህበር( ኦፔክ) ራሷን አግልላ እንደነበረችና እኤአ በ2016 በድጋሚ አባል እንደሆነች አስታውሷል፡፡

የማዕከላዊ አፍሪካቷ ሀገር ባለፈው ዓመት ከኦላም ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር የወይራ ዘይት እና የጫማ ምርቷን ትልክ እንደነበረም ተጠቅሷል፡፡