ደቡብ ሱዳን እጅግ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ እጥረት እንዳጋጠማት ተገለጸ

ደቡብ ሱዳን እጅግ  ከፍተኛ  የሆነ የነዳጅ እጥረት  እንዳጋጠማት ተመለከተ ።   

በእጥረቱ ሳቢያ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የተቋረጠ ሲሆን በሃገሪቱ የሚገኙ ትልልቅ መስሪያ ቤቶችም ተዘግተዋል፡፡ደቡብ ሱዳን በከፍተኛ የነዳጅ እጥረት እየታመሰች ነው፡፡

ለዚህ እጥረት መከሰት ደግሞ የሃገሪቱ ነዳጅ አቅራቢዎች በሙስና መዘፈቅ በምክንያትነት እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡

እጥረቱን ተከትሎም ናይል የተሰኘው ነድጅ አቅራቢ ኩባንያ አንዱን ሊትር ነዳጅ በ110 የደቡብ ሱዳን ፓውንድ በመቸብቸብ ላይ ነው፡፡

ይህም ለአንድ ሊትር የተከፈለ ከፍተኛ ገንዘብ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በሳምንቱ መጀመሪያ የህዝብ ትራንሰፖርት አገልግሎት በመቋረጡና የመንግስት መስሪያ ቤቶች በመዘጋታቸው ዋና ከተማዋ ጁባ ጸጥ ረጭ ብላ ውላለች፡፡

አንዳንድ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደተናገሩት ለኤሌክትሪክ ጀነሬተር የሚሆን ነዳጅ ባለመኖሩ የሚኒስተር መስሪያ ቤቶች ሳይቀሩ በያዝነው ሳምንት ተዘግተዋል፡፡

“ባለፉት ሶስት ሳምንታት በጣም በርካታ መልዕክቶችን ለናይል የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያ ብንልክም አንድ ሊትር ነዳጅ እንኳ ሊሰጡን አልቻሉም ፡፡

ምክንያቱ ደግሞ እኛ ጉቦ ስለማንሰጣቸው ነው ብለዋል ስማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ ባለስልጣን፡፡

ናይል ፔትሮል ኩባንያ ከአጎራባች የአፍሪካ ሃገራት ነዳጅ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚያስገባ ተቋም ሲሆን ወደ አዲሲቷ ሃገር ከሚያሰገባው ነዳጅ ውስጥ አንድ ሶስተኛውን ብቻ በመደበኛ ዋጋው በ22 የደቡብ ሱዳን ፓውንድ ይሸጣል፡፡

የተቀረውን ሁለት ሶስተኛ የሚሆነውን ነዳጅ በጥቁር ገበያ እስከ 160 የደቡብ ሱዳን ፓውንድ ይሸጠዋል፡፡

“አሁን ባለው ሁኔታ 1.5 ሊትር በሚሆን የውሃ ፕላስቲክ ነዳጅን በ220 የሱዳን ፓውንድ እየገዛን ነው፣ ይህም በሊትር 140 የደቡብ ሱዳን ፓውንድ ማለት ነው ሲል አንድ ታክሲ ሾፌር ተናግሯል፡፡

ሜሪ አቻይ የተባለ የጥቁር ገበያ ነዳጅ ነጋዴ እንደሚለው የነዳጅ ዋጋው መናር በምግብ ሸቀጦች ላይ ለተፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡

እንደ አቻይ ገለጻ እሱን ጨምሮ በጥቁር ገበያው ነዳጅ የሚሸጡ ነጋዴዎች ነዳጁን ከከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናት በውድ ዋጋ ነው የሚገዙት፡፡

በአብዛኞቹ የሃገሪቱ ከተሞች 1 ሊትር ነዳጅ በአማካይ 115 የደቡብ ሱዳን ፓዉንድ ይሸጣል፡፡

 ይህም ከመደበኛ ዋጋው ስድስት እጥፍ በላይ ይልቃል፡፡( ምንጭ: ሱዳን ትሪቡን)